Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በጀርመን የነበራቸው ቆይታ ውጤታማ ነበር – ቢልለኔ ስዩም

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጀርመን የነበራቸው ቆይታ ውጤታማ እንደነበር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በጀርመን በተካሄደው “ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ” ጉባዔ ላይ መሳተፉ ይታወቃል፡፡

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያና ጀርመን መሪዎች የተወያዩባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ቢልለኔ በሰጡት ማብራሪያ÷ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

ውይይቱ ከዚህ በፊት መክረውባቸው የነበሩትን የሁለትዮሽ ጉዳዮች የበለጠ ማጠናከር፣ ቀጣናዊ ጉዳዮችንም የበለጠ ተሳስሮ መስራት ላይ ያተኮረ እነደሆነ ነው የገለጹት፡፡

ጀርመን በተለያዩ ዘርፎች እገዛ የምታደርግ ሀገር መሆኗን የገለጹት ሃላፊዋ ፥ በታዳሽ ኃይል፣ በትምህርት፣ በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የበለጠ አብሮ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) በ”ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ” ጉባዔ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለውን ተግባራት፣ የተፈጠሩ ክፍተቶችን እና ማሻሻያዎችን አስመልክተው ሃሳባቸውን ማካፈላቸውን ቢልለኔ ስዩም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑዔል ማክሮን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

በቆይታቸው ከዚህ በፊት መክረውባቸው የነበሩትን ጉዳዮች ለማደስና የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ለማጠናከር በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ መድረኮችም ያላቸውን ሚና ለመጫወት ተወያይተዋል ነው ያሉት፡፡

በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀርመን ቆይታ ስኬታማ እንደነበርም ነው ቢልለኔ ስዩም የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.