Fana: At a Speed of Life!

በብዛት በሴቶች ላይ የሚከሰተው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምንድን ነው?

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሽንት ሥርዓት አካላትን (ኩላሊትን፣ የሽንት ፊኛን እና የላይኛውን እና የታችኛውን የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦዎች የሚያጠቃ ህመም ነው።

አብዛኞቹ ኢንፌክሽኖች የታችኛውን የሽንት ቧንቧዎች እና የሽንት ፊኛን እንደሚያጠቁ የሚገልጹት የሕክምና ባለሙያዎች÷ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ለበሽታው በይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ኢንፌክሽኖች ከሽንት ፊኛ አልፈው ወደ ኩላሊት ከተሻገሩ አሳሳቢ የጤና እክል ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ይገልጻሉ፡፡

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክቶች ምንድን ናቸው?

አልፎ አልፎ ምልክት ላያሳይ ቢችልም÷ በአብዛኛው ግን ቀጥሎ የተጠቀሱትን ምልክቶች እንደሚያሳይ ይታመናል፡፡

• በመጠን አነስተኛ ግን በተደጋጋሚ ሽንት መሽናት፣
• ደመና የመሰለ የሽንት ቀለም፣
• የሽንት ቀለም መቀየር (ለምሳሌ፡- ቀይ፣ ሮዝ፣ ጠቆር ያለ ሽንት፣ ከሽንት ጋር የደም ምልክት መታየት)፣
• ያልተለመደ ጠንከር ያለ የሽንት ሽታ፣
• ማህፀን አካባቢ የሚሰማ የመጫን ህመም (ለሴቶች) ወይም ወንዶች ብልታቸው አካባቢ እና የሽንት ፊኛ አካባቢ የሚሰማ ህመም ናቸው።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

• እንደባለሙያዎች ገለጻ÷ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ ገብቶ በሚራባበት ጊዜ ነው።
• በተፈጥሮ የብልቶች አቀማመጥ ምክንያትም ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭ መሆናቸውን የሚጠቅሱት ባለሙያዎች÷ በተለይም የግብረ- ሥጋ ግንኙነት ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሴቶችን ያጋልጣል ይላሉ፡፡
• ሴቶች ባላቸው የሰውነት አቀማመጥ (Female anatomy) ምክንያት በግብረ- ሥጋ ግንኙነት ወቅት፣ በማህፀን ውስጥ በሚቀመጡ አንዳንድ የወሊድ መከላከያዎች እንዲሁም ሴቶች በሚያርጡበት ጊዜ (Menopause) ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ከፍተኛ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ይገለጻል፡፡
• ጤናማ ያልሆነ የሽንት ቧንቧ ኖሯቸው የሚወለዱ ሕጻናት፣
• የሽንት ቧንቧ መደፈን (በኩላሊት ጠጠር ምክንያት)፣
• የበሽታ መከላከያ ሥርዓት መጎዳት (ለምሳሌ፡- በስኳር በሽታ ምክንያት ተፈጥሯዊው የበሽታ መከላከያ ብቃት እንዲቀንስ በማድረግ ለኢንፌክሽኑ ተጋላጭ ያደርጋል)፣
• አርቴፊሻል የሽንት ቱቦ (ካቴተር) የሚጠቀሙ ታማሚዎች፣
• የሽንት ፊኛ፣ ፕሮስቴት ወይም የኩላሊት ቀዶ ጥገና ማድረግ አጋላጭ መንስኤዎች ናቸው።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሲበረታ የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው ?

የታችኛው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በአግባቡና በጊዜ ካልታከመ ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል ይላሉ፡፡

• ተደጋጋሚ ኢንፌክሽኖች፣
• ከፍተኛ የሆነ የኩላሊት ኢንፌክሽን እና መድከም፣
• ነፍሰጡሮች ላይ ከተከሰተ ደግሞ የሚወለደው ሕጻን መጠኑ ከሚገባው ያነሰ እንዲሆን ወይም ያለጊዜው እንዲወለድ ማድረግ፣
• በተለይም ወደ ኩላሊት ከተዛመተ ለሕይወት አስጊ እና እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መከላከያ መንገዶች ምንድን ናቸው?

• በቂ ውሃ መጠጣት (ውሃ መጠጣት ቶሎ ቶሎ እንዲሸኑ በማድረግ ባክቴሪያው ኢንፌክሽን ሳያመጣ ከሽንት ቧንቧ እንዲወርድ ያደርጋል)፣
• ከግብረ- ሥጋ ግንኙነት በኋላ የሽንት ቧንቧ አካባቢን ማጽዳት፤ ውሃ በመጠጣት ባክቴሪያው እንዲወገድ ማድረግ፣
• የተለያዩ የብልት ማጽጃዎች (እንደ ፓውደርና ሌሎችም ያሉትን) አለመጠቀም። እነዚህ ማፅጃዎች ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ እንዲገባ ዕድል ይፈጥራሉ፣
• በተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚከሰት ከሆነ እና የወሊድ መከላከያ መንገዶችን መቀየር ካስፈለገ የሕክምና ባለሙያ ማማከር፣

ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ ዲያፍራም (Diaphragm) ወይም spermicide-treated ኮንዶሞች ለባክቴሪያ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይገለጻል፡፡

• ህመሙ ሳይፀና ከሐኪም ጋር መማከር እና የተያዘዘ መድኃኒት ካለ በአግባቡ መውሰድ ይመከራል፡፡

ምንጭ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.