Fana: At a Speed of Life!

በሩብ ዓመቱ ከ4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የወጪ እና ገቢ ዕቃዎችን ማጓጓዝ ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የወጪ እና ገቢ ዕቃዎችን ማጓጓዝ መቻሉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

እየተካሄደ በሚገኘው የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ የሚኒስቴሩ የሥራ እንቅስቃሴዎች ቀርበዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)÷ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ምቹ የሕዝብ ትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋት በተደረገው ጥረት ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።

በአንዳንድ የክልል ከተሞች የትራንስፖርት መናኸሪያዎች የዲጂታል አገልግሎት ተጀምሮ ተገልጋዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ የነበረውን እንግልት በመጠኑ የቀነስ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህንንም ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋት እንደሚሠራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አምስት መናኸሪያዎች ላይ የዲጂታል አገልግሎት ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ በጥናት ላይ የተመሠረቱ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

ከሎጂስቲክስ የጭነት ማጓጓዝ እና ማከማቸት ዘርፍ አንጻርም እየጨመረ የመጣውን ገቢና ወጪ በተሳለጠ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡

በሩብ ዓመቱ ከ4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ ወጪ እና ገቢ ዕቃዎችን ማጓጓዝ መቻሉን ጠቁመው፥ ከዚህ ውስጥ 91 ነጥብ 7 ሜትሪክ ቶን ወደ ሀገር ውስጥ የገባ እና 8 ነጥብ 3 ሜትሪክ ቶኑ ደግሞ ወደ ውጭ የወጣ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን ከማሳለጥ አንጻር 59 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነው በመልቲ ሞዳል የተስተናገደ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በኮንቴነር አሽጎ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን የመላክ አገልግሎትም በተሳለጠ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው÷ ቡናን ሙሉ በሙሉ በኮንቴነር አሽጎ መላክ መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ 95 በመቶ የወጪ ገቢ ምርቶች በጂቡቲ ወደብ መስተናገዱን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ የወደብ አማራጮችን የማስፋት ሥራም በመከናወን ላይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ንግግር መጀመሩን እና ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት፡፡

የደረቅ ወደብም ጅግጅጋ ላይ እንዲሁም የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ቶጎ ጫሌ ላይ ለመገንባት የሚያስችል ጥናት ተጠናቋልም ብለዋል፡፡

የላሙ ወደብን ለመጠቀምም ከኬንያ መንግሥት ጋር ውይይቶች መካሄዳቸውን አስታውሰው ይህም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.