Fana: At a Speed of Life!

በሩብ ዓመቱ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩብ ዓመቱ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ቴክኖሎጂ የማላመድና “የግድቤን በደጄ” ስራዎች በቀጣይ በትኩረት እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።

የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሚኒስቴሮች የስራ አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ የውሃ ሃብት አስተዳደርና የኢነርጂ ልማት ስራ አፈጻጸም ተገምግሟል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ÷ በሩብ ዓመቱ በተለይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ በማድረግ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ኤሌክትሪክን ከዋናው መስመር በመሳብ 100 ሺህ አባወራዎች ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

በውኃ አስተዳደር ዘርፍ ተፋሰሶችን በመለየትና የውሃ ሃብት መለኪያ ዘመናዊ ቴክኖለጂዎችን በመጠቀም መረጃ የመሰበሰብ ተግባር መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሩብ አመቱ የኦሞ ጊቤ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ ዳዋ እና ባሮ አኮቦ ተፋሰሶች መሪ እቅድ የወጣላቸው መሆኑን ገልጸው በቀጣይ በሌሎችም ተፋሰሶች ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በድርቅ ተደጋጋሚ በሚጠቁ አካባቢዎች ቴክኖሎጂን የማላመድና በግድቤን በደጄ መርህ የዝናብ ውሃን በመያዝ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.