Fana: At a Speed of Life!

ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሀገር በቀል ተቋም ገርቶ በማሰልጠን ለሀገር ጥቅም ማዋል ይገባል – ሰለሞን ካሳ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሀገር በቀል ተቋም ገርቶ በማሰልጠን ለሀገር ጥቅምና ልማት ማዋል ይገባል ሲሉ የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አማካሪ ሰለሞን ካሳ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚገኝበት ደረጃና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አማካሪ ሰለሞን ካሳ፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በእርሻ፣ በአስተዳደር፣ በትምህርትና በሌሎች በርካታ አገልግሎቶች ላይ እንደሚተገበር ገልጸዋል።

አክለውም የሰው ሰራስ አስተውሎት ለኢትዮጵያ ክፍተትን በመሙላት፣ ወደኋላ ያስቀረን እና ያልተቀላጠፈ ስርዓታችንን ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በዚህ ሂደት አልፈው ከሀገራቸው አልፈው ለዓለም ብዙ ማበርከት ይችላሉ ሲሉም ነው ያነሱት፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት በዓለም ላይ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ብዙ ዘርፎች እንዲወለዱ ምክንያት መሆኑም አንስተዋል፡፡

ዘርፉን እንደ ኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባለ ሀገር በቀል ተቋም ገርቶ በራስ ልክ ማሰልጠንና ለበጎ ተግባር ማለትም ለሀገር ጥቅምና ልማት ማዋል ግድ እንደሚልም ነው የተናገሩት የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አማካሪ ሰለሞን፡፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከእድሜ አንጻር ትንሽ ቢሆንም እየተንቀሳቀሰ ያለው ግን ከእድሜው በላይ እንደሆነ መመልከታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያን በአፍሪካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ግንባር ቀደም የሚያደርጋትን ተቋም እውን ለማድረግ እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ኢ/ር) ናቸው፡፡

እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.