Fana: At a Speed of Life!

ለንደንን ከ2 እጥፍ በላይ የሚበልጥ የበረዶ ግግር ተገምሶ እየሄደ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የለንደንን መጠነ-ሥፋት ከ2 እጥፍ በላይ የሚሆን የዓለማችን ትልቁ የበረዶ ግግር ተገምሶ እየሄደ ነው ተባለ፡፡

የበረዶ ግግሩ በፈረንጆቹ 1986 ላይ ከአንታርክቲክ ባሕር ዳርቻ ተቆርሶ በዌድል ባሕር አካባቢ የቆየ ሲሆን፥ ከመጠኑ ግዝፈት አንጻርም ‘የበረዶ ደሴት’ የሚል ስያሜን ይዞ በአካባቢው ከ30 አመታት በላይ ቆይታ አድርጓል።

የበረዶ ግግሩ ‘የታላቋን ለንደን’ መጠነ ሥፋት ከሁለት እጥፍ በላይ እንደሚበልጥ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

ከ4 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ መጠን እና 400 ሜትር መጠነ ውፍረት ያለው የበረዶ ግግር አሁን ላይ በንፋስ እና በመሬት ውስጣዊ ግፊት ከነበረበት ስፍራ ለቆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተመራማሪዎች እየገለጹ ነው።

አሁን ላይ ግግሩ የአንታርክቲክ ባሕረ ገብ መሬትን ሰሜናዊ ጫፍ እያለፈ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ተመራማሪዎች “ኤ23 ኤ” በሚል ሥያሜ የሚያውቁትን የበረዶ ግግር እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ለበርካታ አመታት በባህር ላይ ሰፍር ዳርቻ የነበረው ግግር እንቅስቅሴ ስጋት እያጫረ መሆኑንም ዘገባው አመላክቷል።

ግግሩ አሁን ከያዘው የጉዞ አቅጣጫ አንጻር በደቡብ ጆርጂያ ዳርቻ ላይ ቢያርፍ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የዓሳ እና የባሕር ወፎች ዝርያዎች የመኖሪያ ምኅዳር እና ብዝኃ-ሕይወት ያቃውሳል የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡

በሚፈጠረው አዲስ ያልተለመደ ምኅዳርም በብዝኃ ሕይወቱ ውስጥ አዲስ የሚፈለፈሉት የዓሳ እና ዐዕዋፍት ዝርያዎች አኗኗር ፣ አመጋገብ ፣ አስተዳደግ እና እንቅስቃሴ እንደሚቀየር ከወዲሁ መላ ምት አስቀምጠዋል።

ሌሎች አጥኚዎች ደግሞ እየተገፋ የሚመጣው የበረዶ ግግር ሥጋት ብቻ ሳይሆን ዕድልም ነው ይላሉ፡፡

በውስጡ የተለያዩ ማዕድናት የያዘ እንደመሆኑ የብዝኃ-ሕይወቱ የምግብ ሠንሠለት እንዲቀጥል አስተዋፅዖ አለውም ነው የሚሉት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.