Fana: At a Speed of Life!

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈው የተገኙ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች በገንዘብና እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም እና በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተላልፈው የተገኙ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች በገንዘብና እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ተገለጸ።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን እና ሚዲያ አባል ኮማንደር ራሄል አብርሃም፥ እንደገለፁት በሁሉም የዞኑ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የአዋጁን የክልከላ ድንጋጌ ለማስከበር ቁጥጥር ሲደረግ ቆይቷል።

ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ በተካሄደው ቁጥጥር ድንጋጌውን ተላልፈው ሰዎችን በማሰባሰብ ተስዝካር፣ ሰርግ፣ ክርስትናና ማህበር የደገሱ ከሁለት ሺህ የሚበልጡ ግለሰቦች ተደርሶባቸዋል።

በተጨማሪም ከሦስት ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ደግሞ የመጫን አቅማቸው በግማሽ እንዲቀንስ የተቀመጠውን ገደብ በመጣስ ጥፋት መፈጸማቸውን ኮማንደር ራሄል አመልክተዋል።

በማስረጃ ተረጋግጠባቸውም በየአካባቢው ፍርድ ቤቶች ቀርበው እንደየጥፋታቸው እያንዳንዳቸው ከ3 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር እና እስከ ስድስት ወራት በሚደርስ ቀላል እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን አስታውቀዋል።

ስለበሽታው አስከፊነት ግብር ኃይሉ ተከታታይ የማስተማር አለፍ ሲልም በህግ ለማስቀጣት ጥረት ቢደረግም አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ቸልተኝነትና መዘናጋት ይስተዋላል።

ከማንደሯ እንዳሉተ በሽታውን ለመግታት የወጣውን የአዋጁን ድንጋጌ የሚጥሱ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ማህበረሰቡም የበሽታውን አስከፊነት በመረዳት አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ እንዲቀሳቀስ እና የመንግስት መመሪያን እንዲያከብርም አሳስበዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት ጓዴ በሰጡት አስተያየት በሽታውን ለመከላከል መንግስት ያወጣውን አዋጅ እንደሚያከብሩ ገልጸው ህጉን በሚተላለፉ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

በዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ሽመልስ መንግስቴ እንዳሉት በአከባቢው አሁንም የጀበና ቡና፣ ካፌና ጠላ ቤቶች ሰዎች እየሰባሰቡ በመሆኑ አስተማሪ ቅጣት እየተወሰደ አይደለም።

“ቫይረሱ አደገኛ በመሆኑ ህግን የማስከበሩ ስራ በተደራጀና ወጥ በሆነ አግባብ መፈፀም ይገባዋል” ብለዋል።

በተመሳሳይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በሆሮ ወረዳ ሻምቡ ከተማ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት የተደነገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተለልፈው የተገኙ 24 ግለሰቦች በገንዘብ እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን የወረዳው የቫይረሱ መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ።

የግብረ ኃይሉ አባል የሆነው የሆሮ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ መገርሣ ዋቆ እንዳስታወቁት በከተማ ግለሰቦቹ በአንድ ቦታ በመሰብሰብ ካርታ ሲጫወቱና ጫት ሲቅሙ በጸጥታ አካላት እጅ ከፍንጅ ተደርሶባቸዋል።

በዚህም ተከሰው ጉዳያቸውን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ መሆናቸውን በማረጋገጥ እያንዳንዳቸው ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ 500 ብር እንደቀጡ የወሰነባቸው መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.