Fana: At a Speed of Life!

የሠራዊቱን ግዳጅ የመፈጸም አቅም በማጎልበት የሀገርን ሰላም ማስከበር ሥራው ይጠናከራል- ሌ/ ጄ ዘውዱ በላይ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ግዳጅ የመፈጸም አቅም በማጎልበት የሕዝብን ሰላምና ደህነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ገለጹ።

ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ ÷የመከላከያ ሠራዊቱን ግዳጅ የመፈጸም ብቃቱን ማጎልበት የዘወትር ተግባር ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ሠራዊቱ ግዳጅ የመፈጸም አቅሙን በማጎልባት የሕዝቡን ብሎም የሀገርን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

ሠራዊቱ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ሁሉ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃትና በድል አድራጊነት እየተሻገረ የሕዝቡን ሰላም እያረጋገጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በቄለም ወለጋ የሸኔ የሽብር ቡድን ሲፈጥር የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም ሠራዊቱ ባካሄደው የሕግ የማስከበር ዘመቻ በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሠራዊቱ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ የተገኘውን ሰላም ለማጽናትና ለማረጋገጥ ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር  በትብብር እየሰራ መሆኑን ሌተናል ጄኔራሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የቄለም ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳደሪ አቶ መንግስቱ ደረሱ በበኩላቸው÷የዞኑ ሕዝብ ባለፉት አራት ዓመታት የሸኔ የሽብር ቡድን በፈጠረው የጸጥታ ችግር ህዝቡ በሰላም እጦት ሲሰቃይ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።

በዞኑ የተገኘውን ሰላም ይበልጥ ለማጠናከር የዞኑ ህዝብና አስተዳደር ከሠራዊቱ ጎን በመሆን እየሰራ መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.