Fana: At a Speed of Life!

ጎግል አገልግሎት ላይ ያልዋሉ አካውንቶችን በተያዘው ሳምንት መሰረዝ ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎግል ኩባንያ ተከፍተው አገልግሎት ላይ ሳይውሉ የቆዩ አካውንቶችን በተያዘው ሳምንት መሰረዝ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

የሚሰሩዙት አካውንቶችም ተከፍተው አገልግሎት ሳይሰጡ ሁለት ዓመትና ከዛ በላይ ጊዜ ያስቆጠሩ አካውንቶች እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡

ውሳኔው በኩባንያው ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን መቀነስ እንደሚያስችል ነው የተገለጸው፡፡

ተዘግተው የቆዩ አካውንቶች ባለ ሁለት ዲጂት የማረጋገጫ ኮዶችን እንደማይወስዱ አረጋግጫለሁ ያለው ኩባንያው÷ ይህም አካውንቶቹን ለመጠለፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ጠቁሟል፡፡

ከባለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮም ደንበኞች ተዘግተው ለቆዩ አካውንቶች የይለፍ ቃል ማስተካከያዎቻቸውን እንዲያዘምኑ የማስጠንቀቂያ መልዕክት መላኩን አስታውሷል፡፡

በሌላ በኩል ከዩቲዩብ፣ከስጦታ ካርዶች እንዲሁም ከዲጂታል ቁሶች ጋር የተገናኙ አካውንቶች እንደማይዘጉ መገለጹን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያው የጎግል አካውንት ተጠቃሚዎች ከሁለት ዓመት አንድ ጊዜ አካውንታቸውን በመክፈት መልዕክት መላላክ ወይም በጎግል የሚለቀቁ ተንቀሳቃሽ ቪዲዮዎችን መመልከት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.