Fana: At a Speed of Life!

ጾታዊ ጥቃትን ለመግታት ባለድርሻ አካላት ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ተጠየቀ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የስነ-ተዋልዶ ጤና ማህበራት ጥምረት ከሼር ኔት ኢትዮጵያ እና ከተመድ የስነ-ህዝብ ፈንድ ጋር በመተባበር በዓለም ለ32ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ የሚታሰበውን ጸረ- ጾታዊ ጥቃት ቀንን አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ -ህዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይ፣ የስፔን አለም አቀፍ ትብብር የኢትዮጵያ ኃላፊ፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች እና የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባላት ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የሴቶችና ህፃናት ሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዘቢዳር ቦጋለ ÷አለም አቀፉ የፀረ ፆታዊ ጥቃት የ16 ቀናት የንቅናቄ መርሃ ግብር “መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አንበል” በሚል መሪ ሃሳብ መጀመሩን ገልጸዋል።

ንቅናቄው የተሃድሶ ማዕከላትን ማጠናከር፣ ለጥቃት ተጋላጮች ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን ማድረግ እና የስራ ዕድሎችን ማመቻቸት እንዲሁም የፆታዊ ጥቃት አስወጋጅ ግብረ ሃይሎችን ማጠናከር የሚያስችል የተቀናጀ የሚዲያ ዘመቻ በማካሄድ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ሁሉም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ፆታዊ ጥቃትን ለመግታት፣ ጥፋተኞች ለህግ እንዲቀርቡ በማስቻል እና ተጎጂዎች የፍትህ እና የማገገሚያ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር በፖሊሲ የተደገፉ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደምትገኝም ገልፀዋል።

የተመድ የስነ ህዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ኮፊ ኩዋሜ÷ ድርጅታቸው ኢትዮጵያ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል እና ለተጎጂዎች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት በዘላቂነት እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።

 

በወንድወሰን አረጋኸኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.