Fana: At a Speed of Life!

የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል እንቅፋት የሚሆኑ አመራሮችን ማጋለጥ እንደሚገባ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮንትሮባንድ እቃዎች ዝውውር የሚሳተፉ የመንግሥት አመራሮችን የማጋለጥና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ገለጹ።

የኮሚሽኑ የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሚኒስትር ዴኤታዎችና የተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ ባለፉት ወራት ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል በተሰራው ሰፊ ስራ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመቱ የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

የኮንትሮባንድ የመከላከልና የቁጥጥር ስራዎች በተከታታይ እየተሰሩ ቢሆንም ችግሩ አሁንም በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ላይ ተፅዕኖ መደቀኑን ጠቅሰዋል።

በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዳይውሉ መረጃ አሳልፈው የሚሰጡ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉትም እንዲለቀቁ የሚያደርጉና በህግ እንዳይጠየቁ የሚሰሩ አመራሮች እንዳሉም ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ለኮንትሮባንድ ዝውውር እጀባ የሚሰጡ አካላት ስለመኖራቸውም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በየአካበቢው ያሉ ኬላዎች የምርት ዝውውርን እያስተጓጎሉና ኮንትሮባንድን እያባባሱ በመሆናቸው እንዲነሱ የተሰጠው አቅጣጫ አለመተግበሩንም ነው ያነሱት።

በየኬላው ችግር የሚፈጥሩ አመራሮችንና ባለሙያዎችን በማጥራት እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም ኮንትሮባንድን መከላከልና መቆጣጠር የሁሉንም ጥረት በመጠየቁ በተፈለገው ደረጃ ውጤት ያለመገኘቱን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.