Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ የኢ-ፍትሃዊነት ድርብ ሰለባ አህጉር ናት – አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ የኢ-ፍትሃዊነት ድርብ ሰለባ አህጉር ናት ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናገሩ፡፡

ዋና ፀሃፊው በ7ኛው የአፍሪካ ህብረት እና የተመድ ኮንፈረንስ ላይ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ጋር የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ አዲስ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ÷ ተመድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አፍሪካ የዓለም ዓቀፋዊ ግንኙነት ፍትህ ትፈለጋለች፣ ምክንያቱም አፍሪካ በዓለም ዓቀፋዊ ግንኙት ስርዓት ውስጥ የመዋቅራዊ ኢፍትሃዊነት ሰለባ ሆና ቆይታለች ብለዋል።

አፍሪካ የፍትህ እጦት ድርብ ሰለባ ሆና ቆይታለች ያሉት ዋና ፀሃፊው÷ የመጀመሪያው የቅኝ ግዛት ኢ-ፍትሃዊነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አሁን ባለው የዓለም የሀይል የበላይነት ምክንያት በአህጉሪቱ የተፈጠረ የኢኮኖሚ ኢ-ፍትሃዊነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በበኩላቸው÷ አፍሪካ በሰላምና ፀጥታ አለመረጋገጥ ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እያሳለፈች ትገኛለች ብለዋል፡፡

አብዛኛው የአፍሪካ ሀገር የሽብርተኝነት ችግር ተጠቂ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

አፍሪካ በኮቪድ-19 ፣ በአየር ንብረት ቀውስ እንዲሁም በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በኢኮኖሚ እየተፈተነች እንደምትገኝ አንስተዋል፡፡

ከተመድ ጋር የተፈረመው አዲሱ ስምምነት ችግሮቹን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ገልፀው÷ ስምምነቱን ህብረቱ በደስታ ይቀበለዋል ማለታቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.