Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለማስተካከል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለማስተካከል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስገነዘበ።

የባንኩ ገዥ ማሞ ምኅረቱ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በ2015 የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን አስታውሰው፤ ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በ6 ነጥብ 5 በማደግ ጠንካራና አበረታች ውጤት እንደተመዘገበ ተናግረዋል።

ባለፉት ሥድስት ወራት ውስጥ የዋጋ ንረቱ በተከታታይ ቅናሽ አስመዝግቧል ያሉት አቶ ማሞ÷ ምንም እንኳን የዋጋ ንረቱ አሁንም ከፍተኛ ቢሆንም ሂደቱ ግን እየቀነሰ መሆኑን አሃዞች ያሳያሉ ነው ያሉት፡፡

ለአብነትም ያለፉትን አራት ወራት መረጃዎች በመስከረም ወር በገመገምንበት ወቅት የኑሮ ውድነቱ በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ከነበረበት 35 በመቶ ገደማ ወደ 27 ነጥብ 7 በመቶ መቀነሱን ዐይተናል ብለዋል፡፡

ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ንረት አሁንም ከ30 በመቶ አለመውረዱን ገልጸው÷ በአንጻሩ የምግብ ነክ ዋጋ ንረት በሩብ ዓመቱ መጨረሻ 26 ነጥብ 1 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ የዋጋ ንረት የቆየ መሠረታዊ ችግር መሆኑን የገለጹት የባንኩ ገዥ÷ አሁን ያለበት አሃዝ ዝቅተኛ ነው ባይባልም ሂደቱ ግን ቅናሽ እያሳየ መሆኑን ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

ከመድኃኒትና ሕክምና አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ያለውን የዋጋ ንረት ለማስተካከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ መንስኤዎች የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች (በተለይም በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የሸቀጥ ዋጋ መጨመር)፣ በትራንስፖርት አውታሮች፣ የሎጂስቲክስ ሥርዓትና የችርቻሮ/የጅምላ ንግድ ተወዳዳሪነት ድክመት እንዲሁም የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን፣ የምርትና ምርታማነት በበቂ ሁኔታ አለማደግ እንደሆኑ አብራርተዋል።

በተጨማሪም የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ልል መሆን እና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው አለመረጋጋት ለዋጋ ንረቱ ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለማስተካከል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አመላክተው፤ እንደ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረጉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ባንኮች የሚሰጡት ብድር ዕድገት ከ14 በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ አስቀምጠናል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ የሚወስደውን ብድር በ75 በመቶ ቀንሰናል ብለዋል፡፡

ባንኩ የተለያዩ የገንዘብ ፖሊሲዎች ላይ ጠንካራ ውሳኔዎችን በማሳለፉም አሁን ላይ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.