Fana: At a Speed of Life!

ስለሄፓታይተስ ምን ያሕል ያውቃሉ?

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሄፓታይቲስ የጉበት ቁስለት በመባል የሚታወቅ ሲሆን ጉበታችን በተላላፊ ቫይረሶች እና ኢ-ተላላፊ አነሳሾች ምክንያት ሲጎዳ እና ሲቆስል የሚመጣ ህመም ነው፡፡

ጉበት በሆድ የላይኛው ክፍል በስተቀኝ በኩል ሲገኝ የንጥረ ነገሮችን ሂደት የሚያስተካክል፣ ደምን የሚያጣራ እና ኢንፌክሽንን የሚዋጋ ወሳኝ አካል እንደሆነ ይገለጻል፡፡

ስለዚህ የጉበት ቁስለት እና መጎዳት ከፍተኛ የሆነ የጤና መታወክ እና ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡

ይህን ህመም አምጪ ከምንላቸው ተላላፊ ቫይረሶች ውስጥ ሄፓታይተስ ቫይረስ ኤ፣ ቢ፣ሲ፣ ዲ እና ኢ ተጠቃሽ ሲሆኑ ፥ አልኮል፣ በመድሃኒቶች መመረዝ እና የሰውነት እራስን በራስ ማጥቃት ኢ-ተላላፊ ከምንላቸው ውስጥ ይካተታሉ፡፡

የሄፓታይተስ ቫይረሶች ሁሉም የጉበት በሽታ ቢያስከትሉም በሕመም ክብደት፣ በስርጭት መጠን፣ በመተላለፊያና በመከላከያ ዘዴዎቻቸው ይለያያሉ።

ሄፓታይተስ ቫይረስ ኤ እና ኢ በቫይረሱ በተበከለ ውሃ እና ምግብ ሲተላለፉ፤ ሄፓታይቲስ ቫይረስ ቢ እና ሲ ደግሞ ቫይረሱን ተሸካሚ በሆኑ ሰዎች ደም፣ የሴት ብልት ፈሳሽ፣ የዘር ፈሳሽ እና የተለያዩ የሰውነት ፈሳሾች እንደሚተላለፍ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የሄፓታይተስ ህመም ምልክቶች እንደ መንስኤዎች እና ህመም ክብደት በጥቂቱ ቢለያይም የሚከተሉትን ያካትታል።

• ድካም
• የጉንፋን መሰል ምልክቶች
• የሽንት መጥቆር
• የሰገራ ቀለም መንጣት
• የሆድ ህመም
• የምግብ ፍላጎት ማጣት
• የክብደት መቀነስ
• የቆዳ እና የአይኖች ቢጫ መሆን

ሄፓታይተስን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ፥ የሄፓታይተስ ቫይረሶችን ለመከላከል የሚረዱ ብዙ ክትባቶች አሉ። ሆኖም ግን እስካሁን የሄፓታይተስ ቫይረስ ሲ እና ኢ ክትባቶች የሉም።

ከክትባት በተጨማሪም ለቫይረሱ የመጋለጥ እድልን መቀነስ እና ሌሎች ህመሙን የሚቀሰቅሱ እንደ አልኮል እና የመድሃኒት መመረዝን መቀነስ አስፈላጊ የመከላከያ እርምጃ እንደሆነም ይጠቀሳል።

ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ምግብን አብስሎ መመገብ፣ የግል እቃዎችን በጋራ አለመጠቀም፣ በጾታዊ ግንኙነት ወቅት ኮንዶም መጠቀም እና ከሰውነት ፈሳሾች ንክኪ መቆጠብ እንደሚገባም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.