Fana: At a Speed of Life!

የልማት ድርጅቶች በሩብ አመቱ ከ249 ቢሊየን ብር ብላይ ገቢ ማግኘታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ249 ቢሊየን ብር ብላይ ገቢ ማግኘታቸው ተገለጸ።

ድርጅቶቹ በዓለም አቀፍ የትርፋማ ቢዝነስ ሞዴል እንዲመሩ የለውጥ ሥራዎች መከናወኑን ተከትሎ ወደ ከፍተኛ ትርፋማነት መሸጋገራቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሀብረቢ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በ2015 በጀት ዓመት ከ924 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከልማት ድርጅቶቹ የተገኘው ገቢ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ43 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውንም ነው ያብራሩት፡፡

በሌላ በኩል የስኳር ፋብሪካዎች፣ ፐልፕና ወረቀት እንዲሁም የማዕድን ኮርፖሬሽን አሁንም በኪሳራ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፥ የኪሳራ መጠናቸው ግን ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

የስኳር ፋብሪካዎች በ2014 በጀት ዓመት ያስመዘገቡት ኪሳራ 5 ቢሊየን ብር እንደነበር አስታውሰው÷ በ2015 በጀት ዓመት ግን ወደ ግማሽ ቢሊየን ብር ማውረድ ተችሏል ነው ያሉት።

እነዚህን ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ ከዕዳ በማላቀቅ ወደ ትርፋማነት ለማሸጋገር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ቦርድ የኩባንያ የሽግግር ፕሮግራም ማጽደቁን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች አጠቃላይ ኃብት ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር በላይ መድረሱ ታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.