Fana: At a Speed of Life!

የሳንባ ምች ምልክቶች፣ መከላከያ መንገድና ህክምናው

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳንባ ምች ከየትኛዉም በሽታ በባሰ ሁኔታ በርካታ ህፃናትን ለሞት የሚዳርግ ቢሆንም ዛሬም ትኩረት የተነፈገው በሽታ ሆኖ ይገኛል፡፡

በሽታው ከአንድ ወር እስከ አምስት አመት ዕድሜ ላላቸዉ ህፃናት ቁጥር አንድ የሞት መንስኤ መሆኑም ነው የሚገለጸው፡፡

በሳንባ ምች የሚቀጠፉ አብዛኛዎቹ ህፃናት የሳንባ ምችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማከም የሚችሉ ግንባር ቀደም የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ዕድሉ በሌለባቸውና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባላቸዉ አካባቢዎች የሚወለዱ መሆናቸው ነው የሚነገረው፡፡

ከሳንባ ምች በትንፋሽ፣ በሽታዉ ያለበት ሰዉ በሚያስልበትና በሚያስነጥስበት ጊዜ በሚወጡ ተህዋሲያን ይተላለፋል፡፡

የሽታዉ ምልክቶች ሳል፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ ለመተንፈስ መቸገር፣ ትኩሳት፣ የደረት ህመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡

የሳንባ ምች መከላከያ መንገዶች ምንድናቸው?

ህፃናትን ከሳምባ ምች በመከላከል ህይወትን መታደግ እንደሚቻል ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም ህፃናትን በማስከተብ፣ ህፃናትን ከመመጉብ በፊት የእጅ ንፅህናን በመጠበቅ፣ የዉሃ የንፅህናና የመፀዳጃ ቤት አገልግሎቶችን በማሻሻል የሳንባ ምች አምጪ ከሆኑ ተያያዥ የበሽታ መንስኤዎች መከላከል ይቻላል፡፡

የቤት ዉስጥ የአየር መበከልን ጪስ ባለማጨስና መስኮት በመክፈት በመከላከል፣ የአየር መበከልን በመቀነስ የሳንባ ምች አምጪ የሆኑ ተያዥ ችግሮችን በመቅረፍና የክትባት ሽፋን ተደራሽነትን በማሳደግ በሽታውን መከላከል ይቻላል።

በተጨማሪም የማህበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር ማህበረሰቡ ስለ ሳምባ ምች ያለዉን ግንዛቤ በማሳደግና በቤት ዉስጥ የሚያደርጉት እንክብካቤ አስተማማኝ እንዲሆን በማስቻል በሽታውን መከላከል ይቻላል፡፡

የሳንባ ምች ህክምና

ህፃናት በሳንባ ምች በሽታ ሲያዙ በወቅቱ የህክምና አገልግሎት ካገኙ በህፃናት ላይ ሊከሰት የሚችለዉን ሞት 36 ከመቶ ያህሉን መቀነስ ይቻላል።

በቀበሌ ወይም በማህበረሰብ ደረጃ ተደራሽ የሆነ የሳንባ ምች በሽታን መርምሮ (ለይቶ በማወቅ) ፈዋሽ በሆነ ፀረ-ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) የማከም አገልግሎት ይሰጣል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.