Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮናቫይረስን ለማከም ይረዳል በተባለው ሃይድሮክሲክሎሮኪን የወባ መድሃኒት ላይ የሚያደርገውን ሙከራ አቋረጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮናቫይረስን ለማከም እንደሚረዳ የተነገረው ሃይድሮክሲክሎሮኪን በተባለው የወባ መድሃኒት ላይ ሲያደርግ የነበረውን ሙከራ አቋረጠ።

ሙከራው የተቋረጠው መድሃኒቱ ከደህንነት ጋር ተያይዞ አደጋ ሊያደርስ ይችላል በሚል ስጋት እንደሆነም ድርጅቱ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ሃይድሮክሲክሎሮኪን በተባለው የወባ መድሃኒት ላይ በተለያዩ ሀገራት የተጀመሩ ሙከራዎችም የሚቋረጡ መሆኑንም የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በመድሃኒቱ ላይ የሚደረገው ሙከራ እንዲቋረጥ የተደረገውም መድሃኒቱ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የተያዙ ሰዎችን የመሞት እድል ይጨምራል የሚል በቅርብ የተሰራ ጥናት በመጠቆሙ እንደሆነም ታውቋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ የወባ መድሃኒት ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ይረዳል ሲሉ የተደመጡ ሲሆን፥ “ሃይድሮክሲክሎሮኪን የተባለውን እየወሰድኩ ነው” ማለታቸውም ይታወሳል።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ቢሉም የዘርፉ ባለሙያዎች የፀረ ወባ መድሃኒት የኮሮናቫይረስን ከማከም ይልቅ የጤና የሚያስከትለው ጉዳት ያመዝናል፤ የልብ ህመምን ሊያስከትል ይችላልም ብለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በላንሰንት ሜዲካል ጆርናል ላይ የወጣ የጥናት ውጤትም፥ በሃይድሮክሲክሎሮኪን የኮቪድ ታማሚዎችም ማከም ምንም ውጤት እንደሌለውና፤ ከማዳን ይልቅም በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል የገቡ ሰዎችን የሞት ቁጥር ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል አመላክቷል።

የላንሰንት ጥናት ላይ 96 ሺህ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች የተሳተፉ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 15 ሺህ ታማሚዎች ሃይድሮክሲክሎሮኪን መድሃኒት እንዲወስዱ በማድረግ ነው ጥናቱ የተካሄደው።

በጥናቱም መድሃኒቱን በወሰዱት እና ባልወሰዱት መካከል በተደረገ ማነፃፀር፤ ሃይድሮክሲክሎሮኪን መድሃኒትን የወሰዱ ታማሚዎች ሆስፒታል እያሉ ህይወታቸው የማለፍ አድል በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን እና የልብ ምት መዛባት ችግር እንደታየባቸውም አመላክቷል።

ጥናቱ በማከልም “ሃይድሮክሲክሎሮኪን” የወባ በሽታን ለማከም በጣም ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ለኮቪድ 19 ህክምና ላይ ለማዋል ምንም አይነት ክሊኒካል ሙከራ አለመደረጉን እና እንደማይመከርም አስታውቋል።

ለኮሮናቫይረስ መድሃኒት ለማድገኘት በርካታ ክልኒካል ሙከራዎችን እያደረገ ያለው የዓለም ጤና ድርጅትም፥ ሰዎች ራሳቸውን ለማከም በሚል ሃይድሮክሲክሎሮኪን መውሰዳቸው አሳሳቢ መሆኑን እና ራሳቸውንም ለከፋ ጉዳት ሊዳርጉ ይችላሉ ሲል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።

ድርጅቱ በትናንትናው እለትም ሃይድሮክሲክሎሮኪንን ሙከራ ከሚደረግባቸው ዝርዝር መድሃኒቶች ውስጥ መውጣቱን ድርጅቱ አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በማከልም ሀገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የጣሉትን አንቅስቃሴ ገደብ ማላላትና ማንሳት መጀመራቸውን ተከትሎ ሁለተኛ ዙር የቫይረሱ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል ሲል አሳስቧል።

አሁንም ቢሆን አሜሪካን ጨምሮ በአውሮፓ ያሉ ሀገራት ቫይረሱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የምርመራ እና የክትትል ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብሏል ድርጅቱ።

ምንጭ፦ bbc.com

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.