Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየጨመረ በመሄዱ የሚወሰዱ እርምጃዎችና ስራዎች እየጠበቁ እንደሚሄዱ መንግስት ገለፀ 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየጨመረ እየሄደ በመሆኑ የሚወሰዱ እርምጃዎች እና ስራዎች እየጠበቁ እንደሚሄዱ መንግስት ገለፀ።

የኮቪድ19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር የሚኒስቴሮች ኮሚቴ አስተባባሪ ሴክሬታሪያት የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ኮሚቴው ትናነት ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ አስመልከተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ የኮሮና ወረርሽኝ እስካሁን ያለበትን ሁኔታ፣ ያስከተለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅኖ በዝርዝር መወያየቱን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት በሀገሪቱ በተለይ ባለፉት ሶስት ቀናት የታየው ውጤት የተለየ መልክ መያዙንና የመመርመር አቅማችን በጨመረ ቁጥር ቫይረሱ የሚገኝበት ሰው ቁጥር እንደሚጨምር ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ አሳሳቢና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ያሳያል ብለዋል።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ ስርጭቱ በአዲስ አበባ ከፍ ማለቱና በመላው ሀገሪቱ ያለውን አንድምታ ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል።

በአዲስ አበባ አራዳ፣ አዲስ ከተማና ልደታ ክፍለ ከተሞች የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት ከፍ ያለባቸው ክፍለ ከተሞች መሆናቸው ተለይተዋል ነው ያሉት።

የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት በመላው የሀገሪቱ ክፍል አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ኮሚቴው ተወያይቷል።

መንግስት አካባቢዎችን በመለየት ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ከትናንት ጀምሮ ራሱን የቻለ ግብረ ሃይል ተቋቁሞለት ወደ ስራ እንዲገባ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው ያመለከቱት።

አሁንም መሸበር መስጋት ሳያስፈልግ የተሟላና ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተናግረዋል።

ከምንም በላይ የግል ንፅህናን ከመጠበቅ ጀምሮ አፍና አፍንጫን በንፁህ ጨርቅ በመሸፈንና አካለዊ እርቀትን በመጠበቅ ወረርሽኙን መከላከል ግዴታ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.