Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ከመፍጠር በተጓዳኝ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው – አህመዲን ሙሀመድ (ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 23 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር በተጓዳኝ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን ሙሀመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

አህመዲን ሙሀመድ (ዶ/ር) የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ ስር የሚመራው ኮማንድ ፖስትም በክልሉ አዲስ የተደራጀውን አመራር በማገዝ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በክልሉ ከላይ ጀምሮ እስከ ቀበሌ የተዋቀረው አመራር በተቀናጀ መልኩ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ዘላቂ ሰላም የመፍጠርና ልማትን የማስቀጠል እንዲሁም በየሴክተሩ የህዝብን ጥያቄዎች በሂደት የመመለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

አዲስ የተደራጀው የክልሉ የፖለቲካና የጸጥታ አመራር በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጁ ሥልጠናዎች ላይ በመሳተፍ ህዝብን ለማገልገል የሚያስችል የተነሳሽነት ልምድ ማግኘቱንም አንስተዋል።

በመድረኮቹ በመልካም አስተዳደር፣ በልማት፣ በኑሮ ውድነት፣ በሰላምና ደህንነትና ሌሎችም ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን በቅጡ በመረዳት ወደ ተግባራዊ ምላሽ መገባቱንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር በተጓዳኝ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የክልሉን ዘላቂ ሰላም በማጽናት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ህዝቡ እገዛና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.