Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ ከ1 ሺህ 600 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ ከ1 ሺህ 600 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እንዳስታወቁት፥ በኦሮሚያ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ከተግባራቱ መካከልም በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር እና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተጠቃሽ መሆኑንም አንስተዋል።

ግንዛቤ በመፍጠር ዘርፍ የሚመለከታቸው አካላትን በማሳተፍ በተሰራው ስራ እስካሁን 35 ሚሊየን 425 ሺህ 116 ለሚሆኑ ሰዎች የፊት ለፊት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መሰራቱን አስታውቅዋል።

ሆኖም ግን በተጠበቀው መልኩ የባህሪ ለውጥ እየመጣ አይደለም ያሉት አቶ አዲሱ፥ የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሀብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት እየተስተዋለ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ ረገድ ያለውን ጉድለት ለመፍታት ግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ አዲሱ ገልፀዋል።

የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ1 ሺህ 600 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመግለፅ፤ ከእነዚህም 933 ላይ ክስ ተመስርቶ በገንዘብ እና በቀላል እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል ብለዋል።

ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ የንግድ አካላትንም ምክር ከመስጠት እና ከማስተማር ጎን ለጎን የተለያዩ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም አቶ አዲሱ ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ባሳለፍነው ሳምንት 20 ሺህ 834 የንግድ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ያሉ ሲሆን፥ 409 ነጋዴዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

የወጣውን መመሪያ በመጣስ ትፍር የጫኑ፣ ከታሪፍ በላይ ያስከፈሉ እና ከተፈቀደላቸው የአገልግሎት ዘፍር ውጪ ሲሰሩ በተገኙ አሽከርካሪዎች ላይም የተለያዩ ህጋዊ እርምጃዎች እንደተወሰደባቸውም ገልፀዋል።

በዚህም በ27 ሺህ 345 ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 263 ተሽከርካሪዎች መታሰራቸውን እና በአጠቃላይ ከ19 ሚሊየን 141 ሺህ 500 ብር በላይ በገንዘብ ተቀጥተዋል ብለዋል።

በቀጣይም ህዝቡን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመጠበቅ ሲባል ግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥለም አቶ አዲሱ አረጋ ገልፀዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.