Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ  የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ምሳሌ የሚሆን ነው – ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ  የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል በራሷ አቅም እያደረገችው ያለው ጥረት ለቀጣናው ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዱባይ ውስጥ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መካነ ርዕይ /ፓቪሊዮን/ ጎብኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅት÷ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱ መሆናቸውን ተናግረው ይህን ካልተከላከልን ቀጣናውን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያጠቃ እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡

በዚህም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላካል የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ  ያሉት ወርቅነህ (ዶ/ር) ኢትዮጵያም ለቀጣናው ብሎም ለዓለም ያቀረበችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ  የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል በራሷ አቅም ገንዘብ ሳትለምን እያደረገችሁ ያለው ጥረት ለቀጣናው ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

ይህም ትልቅ ጥረት እና ለውጥ  መሆኑን አንስተው፤ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን እሰጠች መሆኑን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥም በከፍተኛ ደረጃ እየተሳተፈች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መካነ ርዕይ /ፓቪሊዮን/  ውስጥ ያለው መልዕክት ሀገሪቱ በታዳሽ ኃይል ላይ ምን ያህል ትኩረት አድርጋ እንደምትሰራ የሚያሳይ፤ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ምን ያህል የህዝብ ንቅናቄ እንደፈጠረች እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የሚሣይ ነው ያሉት ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ይህ እንቅስቃሴ ወደፊትም እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.