Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያና በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልሎች በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ለመምህራን የእውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና የተሰጠ ሲሆን÷ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል በየደረጃው የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገልጿል፡፡

የቢሮ ሀላፊው ቶላ በሪሶ (ዶር) እንደገለፁት÷ ለተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆን እንደምክንያትነት የሚጠቀሰው በየደረጃው ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት አንፃር አለመሰራቱ ነው።

በክልሉ 600 እና ከዚያ በላይ ውጤት ላስመዘገቡ 37 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችና 1 የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ በድምሩ ለ38 ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷል።

በሌላ በኩል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ሁሉንም ተማሪዎቹን ላሳለፈው የሀይራንዚ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን የምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር÷ በ2015 ዓ.ም የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ከ224 ሚሊየን ብር በላይ ከባለሃብቱና ከአርሶ አደሩ በማሰባሰብ ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ 43 የሁለተኛ ደረጃና 356 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ከ269 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚገኙ በመርሐ ግብሩ ተገልጿል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና የደረጃ ተማሪዎችን በልዩ ሁኔታ በትኩረት ለማስተማር የሀይራንዚ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በስልጤ ልማት ማህበር በ2007 ዓ.ም ተቋቁሞ ተማሪዎችን እየተቀበለ ማስተማር እንደጀመረም ተጠቅሷል፡፡

ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ተማሪዎቹን በከፍተኛ ውጤት እያሳለፈ እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን÷ በ2015 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም በሀገር አቀፍ ደረጃ አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል ተብሏል፡፡

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹክረላ አወል÷ ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የቻለ ነው ብለዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ 112  ተማሪዎች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን÷ 624 ከፍተኛ እና 450 ዝቅተኛ ውጤት ተመዝግቧልም ነው የተባለው።

በዘመን በየነ፣ ሳሙኤል ወርቃየሁ እና ለሊሴ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.