Fana: At a Speed of Life!

የባህርዳር ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል በትኩረት እንደሚሠራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህርዳር ከተማ አሁን ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል በትኩረት እንደሚሠራ የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

የባሕርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በወቅተዊ ጉዳይ በሰጡት ማብራሪያ÷ በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ከተማዋ በችግር ውስጥ እንደነበረች አስታውሰዋል።

ችግሩ የከተማዋን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መጉዳቱን አንስተው÷ ችግሮችን ለመፍታት ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

የተፈጠረው የሰላም እጦት የበለጠ እንዳይባባስ በመስራት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መደበኛ አገልግሎት እንዲሠጡ መደረጉንና ጥያቄዎችንም ለመፍታት በዕቅድ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ያደሩ የዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው÷ በከተማዋ የተደራጁ ከ800 በላይ ማህበራት የግንባታ ፈቃድ እንዲሠጣቸው መደረጉን ገልጸዋል።

ይሄም ከ21 ሺህ በላይ አባወራና እማወራዎችን የቤት ባለቤት የሚያደርግ እና የቆዬ ጥያቄን የፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ለሚኖሩ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እየተሠጠ መሆኑን በመግለጽ፤ የከተማ አስተዳደሩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን አመልክተዋል።

አብዛኛዎቹ ችግሮች ታውቀውና ተለይተው ያደሩ መሆናቸውን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው÷ ችግሮችን በውይይት መፍታት አዋጭና አትራፊ ነው ብለዋል፡፡

ከማህበረሰቡ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ወንድም ወንድሙን መግደል አይገባም፣ የጋራ ጥያቄዎችን በጋራ መፍታት ሲቻል፣ በተለያየ ጎራ ተሰልፎ መጫረስ አስፈላጊ አይደለም የሚል ሀሳብ ጎልቶ መውጣቱንም አንስተዋል።

የከተማዋንና የክልሉን እንቅስቃሴ እንዲታወክ ለማድረግ የሚሠሩ አካላትን በጋራ ሆኖ ማረም ይገባልም ነው ያሉት።

ለአማራ ሕዝብ እቆረቆራለሁ የሚል ሁሉ ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት እንዲያወግዝም ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

የሃይማኖት አባቶች ለሰላም እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በመግለጽ ለሰላም ሁሉም ነዋሪ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ግጭት ምጣኔ ሃብትን ያወድማል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው÷ አንዳንድ ባለሀብቶች የባንክ እዳ መክፈል መቸገራቸውን፣ ሠራተኛ ለማሰናበት መገደዳቸውን አንስተዋል።

ባለሀብቶች በሰላም ሃብት እንዲያፈሩ ለሰላም አወንታዊ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ጠቅሰው÷ ልማትን ሊያስተጓጉል የሚችልን አካሄድ በጋራ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.