Fana: At a Speed of Life!

አመራሩ ከስልጠናው ያገኘውን ዕውቀት በመተግበር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅበት ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አመራሩ ከስልጠናው ያገኘውን ዕውቀት፣ ልምድና ክኅሎት ይዞ በአካባቢው ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አዳም ፋራህ አስገነዘቡ።

አቶ አደም ”ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሐሳብ በጂንካ የስልጠና ማዕከል እየተሰጠ በሚገኘው የመንግሥት አመራር አባላት የዐቅም ግንባታ ስልጠና ላይ እንዳሉት፥ በተከታታይነት እየተሰጠ ያለው ስልጠና በመንግሥት አመራሩ የአመለካከት፣ የአስተሳሰብ፣ የክኅሎትና የተግባር አንድነት እንዲኖር ያደርጋል።

በሀገሪቷ የተጀመረውን የለውጥ፣ የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ዐቅም የሚሆን አመራር እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡

የዐቅም ግንባታ ስልጠናው በዋናነት አራት ፋይዳዎች እንዳሉት ያነሱት አቶ አደም÷ በሀገራዊ እሳቤዎች፣ እስካሁን በተመዘገቡ ሀገራዊ ስኬቶችና በሂደት በገጠሙን ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ሊገጥሙን የሚችሉ ስጋቶች እና መሻገሪያ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ መግባባት መፍጠር ትልቁ ግቡ ነው ብለዋል።

አመራሩ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስፈልጉትን ዕውቀቶች፣ ክኅሎቶችና ልምዶች የሚገበይበት ምቹ አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል።

ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎላ መልኩ እየተሰጠ ያለው የዐቅም ግንባታ ስልጠና የእርስ በርስ ትውውቅንና መተማመንን በመፍጠር ለችግሮች የጋራ መፍትሔ የማምጣት ሁኔታዎችን መፍጠሪያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ስልጠናው በተናጠል ከሚደረግ ጉዞ ይልቅ የተጠናከረ አንድነት እንዲኖረን ከማድረግ አንጻርም ዕገዛው የጎላ መሆኑ ታምኖበት እየተሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል።

የስልጠናው ተሳታፊም ከስልጠናው ያገኘውን ዕውቀት፣ ልምድና ክኅሎት ይዞ በአካባቢው ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ራሱን ዝግጁ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመሆኑም አመራሩ በየጊዜው በመማርና በማንበብ እንዲሁም አዳዲስ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማመንጨት ማሕበረሰቡን የሚጠቅም ሥራ መሥራት አለበት ነው ያሉት።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.