Fana: At a Speed of Life!

ቡና አብዝቶ መጠጣት ከጤና አንጻር እንዴት ይታያል?

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቡና በቀን እስከ ሦስት ሲኒ መጠጣት ለንቃት ፣ ሥራን በአግባቡ ለመሥራት እና ለጤና የመጥቀሙን ያህል ከዚህ መጠን ካለፈ የሚያስከትለው ጉዳት እንዳለ ዶክተር ከበደ ይልማ ይናገራሉ።

ለምሳሌ ጤናማ ነፍሠ-ጡር ሴቶች በቀን ከአራት ሲኒ በላይ ቡና የሚጠጡ ከሆነ ÷ የፅንስ መጨናገፍ ፣ ክብደቱ ያነሰ ፣ የመወለጃ ጊዜው ያልደረሰ ልጅ የመውለድ እና መሠል ችግሮች ሊከሰቱባቸው እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡

ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ደግሞ የማስመለስ ፣ የመበሳጨት ፣ የተዛባ የአተነፋፈስ ሥርዓት እና ተያያዥ የጤና እክሎች ልጁ ላይ ሊያጋጥሙ እንደሚችልም ዶክተር ከበደ ይልማ ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው ሴቶች የሚጠጡትን የቡና መጠን ሐኪም በማማከር መወሰን አለበት ነው የሚሉት።

ሌላው የምታጠባ ሴት ከአንድ እስከ ሁለት ሲኒ ብቻ መጠጣት እንዳለባት ይመክራሉ፡፡

ከዚህ በላይ አብዝታ የምትጠቀም ከሆነ ቡና ውስጥ ያለው አነቃቂ ንጥረ-ነገር (ካፌይን) በጡት ወተት አማካኝነት ወደ ሕፃኑ ስለሚደርስ እና ሕፃኑ ንጥረ-ነገሩን እየለመደው ስለሚሄድ ጡት ባልጠባ ጊዜ እንዲነጫነጭ ያደርገዋል ይላሉ፡፡

አንድ ጊዜ የድባቴ በሌላ ጊዜ ደግሞ ከፍተኛ የደስታ ስሜት የሚስተዋልባቸው ሰዎች (ባይ ፖላር ዲስ ኦርደር) ያለባቸው ሰዎች “ሙድ ስታብላይዘር” መድሐኒት እንዲወስዱ በሐኪም ይመከራል እንጂ ቡና መጠጣት የለባቸውም፡፡

የልብ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ቡና መጠጣት የለባቸውም የሚሉት ዶክተር ከበደ፥ የሚጠጡ ከሆነ የሕመማቸውን ደረጃ ከፍ እያደረጉ መሆኑን ሊያውቁ ሊገነዘቡ እንደሚገባም ይጠቅሳሉ፡፡

በመጨረሻም ቡና አብዝቶ መጠጣት በአጥንታችን ውስጥ ያለውን የካልሲየም መጠን በሽንት እንዲወገድ ስለሚያደርግ የአጥንት መሳሳት እንደሚያስከትልም አስረድተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.