Fana: At a Speed of Life!

የሲንጋፖር ተማሪዎች በሒሳብ፣ በሳይንስና በንባብ ቀዳሚ ደረጃ መያዛቸው ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲንጋፖር ተማሪዎች በሒሳብ፣ በሳይንስ እና በንባብ ቀዳሚ ደረጃ መያዛቸውን 38 አባል ሀገራት ያሉት የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት (ኦኢሲዲ) ጥናት አስታውቋል፡፡
 
ተማሪዎች እውቀታቸውን እና ክህሎቶቻቸውን በተጨባጭ በዓለም ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምን ያህል እንደሚጠቀሙ ለመለካት ዓለም አቀፍ የመመዘኛ ጥናት ተካሂዷል፡፡
 
በዚህም ዕድሜያቸው አስራ አምስት ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል።
 
ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ከ149 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ከ15 የግል ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 6 ሺህ 606 ተማሪዎች ውስጥ ሲንጋፖር በ2022 ዓለም አቀፍ የተማሪዎች ምዘና መርሐ ግብር (ፒሳ) በሒሳብ፣ ሳይንስ እና ንባብ 1ኛ ደረጃን መያዟ ተመላክቷል፡፡
 
ሲንጋፖርን ተከትለው አየርላንድ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡
 
በድርጅቱ በየሦስት ዓመቱ የሚካሄደው ጥናት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት መዘግየቱም ተጠቅሷል።
 
ውጤታቸው በ2018 ከነበረው ጋር ሲነፃፀር፣ በፒሳ 2022 የተሳተፉ የሲንጋፖር ተማሪዎች በሒሳብ ውጤታቸውን አስጠብቀው በሳይንስ ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩ ሲሆን በንባብ ግን መጠነኛ መቀነስ ማሳየታቸው ተገልጿል።
 
የሲንጋፖር ትምህርት ሚኒስቴር በሀገሪቱ ተማሪዎች ላይ ያለው የንባብ መቀነስ በሌሎች በርካታ ሀገራት ካሉ እኩዮቻቸው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አንስቷል፡፡
 
ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በንባብ ልምድ ላይ ያለውን ለውጥ የሚያንፀባርቅ ነው ሲል መግለፁን ዘ ስትሬይትስ ታይምስ ዘግቧል።
 
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.