Fana: At a Speed of Life!

በመደመር ፍልስፍና ገዥ ትርክቶችን በማጎልበት አንድነትን ማጠናከር ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመደመር ፍልስፍና ገዥ ትርክቶቻችንን በማጎልበት አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር ክፍል ሃላፊና የኮምቦልቻ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ ተተካ በቀለ ገለፁ።

በኮምቦልቻ ከተማ የ4ኛው ዙር የአመራር አባላት ስልጠና የማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

አቶ ተተካ በቀለ በማጠናቀቂያ መርሐ-ግብሩ ላይ እንደገለፁት፥ በተሳሳተ ትርክት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ ቡድኖችን በጋራ መመከት ይገባል።

ለዚህም አመራሩ የጠራና የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረው በየደረጃው የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ተለዋዋጭ ሁኔታውን ተገንዝቦ ለህብረተሰቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና አቅም በመጠቀም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት በትጋት መሰራት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የወጣቶች ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ፈዲላ ቢያ በበኩላቸው፥ ስልጠናው አመራሩ የአካባቢውን ፀጋና ሀብት ለይቶ እንዲያውቅና በአግባቡ መጠቀም እንዲችል እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም የእርስ በእርስ ግንኙነቱን በማሳደግ በጋራ ጠንካራና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት እንደሚያግዝ በመጥቀስም፥ ጠንካራ አንድነትን በመፍጠር የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን አንስተዋል።

ያገኙትን እውቀት ተጠቅመውም በመደመር ፍልስፍና የጋራ ትርክቶችን በማጎልበት ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራር አባላትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.