Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ያስገነባውን የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ አስመርቋል፡፡

የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደርቤ አስፋው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ÷ ባንኩ በብዙሃን ተመስርቶ ሁሉን አካታች የሆነ የፋይናንስ ስትራቴጂ ቀርፆ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ፡፡

“በዛሬው ዕለት ያስመረቅነው የባንኩ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ህንፃም የባንኩ ቋሚ ንብረት ማፍራት ውጤት ማሳያ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ተበትነው የነበሩ የባንኩ የስራ ክፍሎችን በአንድ ላይ የሰበሰበ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

የባንኩ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ 15 ወለል እንዲሁም ከምድር በታች 4 ወለሎች እንዳሉት የተገለፀ ሲሆን÷ለህንጻ ግንባታውም ከ850 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል ነው የተባለው፡፡

ከምድር በታች ባሉ አራት ወለሎች 24/7 የሚሰራ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት እና በአውቶሜት ታግዞ 66 መኪኖችን ማቆም የሚችል የፓርኪንግ ቦታ ያለው እንደሆነም ተናግረዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ፍቃዱ ድጋፌ፣ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አባዱላ ገመዳ እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.