Fana: At a Speed of Life!

በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ መክሸፉን የጋራ ግብረ- ኃይሉ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ መክሸፉን የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል፡፡

የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል እንዳስታወቀው÷ ፅንፈኛ ኃይሎች እና የሽብር ቡድኖች በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በትጥቅ የታገዘ ግፍና ግድያ በመፈፀም እንዲሁም የጸጥታ ችግሮችን በመፍጠር የኅብረተሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያወኩ ይገኛሉ፡፡

ፅንፈኛ ኃይሎችና የሽብር ቡድኖች በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች እየፈፀሙት ያለውን ፀረ- ሰላም እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የዓለም-አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ወደ ሆነችው አዲስ አበባም በማስፋፋት በሚፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሀገሪቱን የትርምስ ቀጣና እናደርጋለን በማለት የጥፋት ሴራዎችን አቅደው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ በተደረጉ የመረጃ ስምሪቶች ተረጋግጧል ብሏል መግለጫው፡፡

በዚህ መነሻነትም ወደ ከተማዋ የታጠቁ ኃይሎችንና ቡድኖችን አስርጎ የማስገባት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን÷ሰልፍ አናካሂዳለን በሚል ሰበብና ሽፋን ሁከትና ግርግር በመፍጠር ንፁሃንን ኢላማ ያደረግ የሽብር ጥቃት የመፈፀም የተጠና ዕቅድ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር መታወቁን የጋራ ግብረ -ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡

ይሄንን እኩይ የጥፋት ሴራ ለመፈጸም ተልዕኮ የወሰዱ 97 ተጠርጣሪዎች በተከናወኑ ኦፕሬሽኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቋል፡፡

ፅንፈኛ ኃይሎችና ቡድኖች ከዚህ የጥፋት መንገዳቸው እንዲመለሱ ችግሮችና አለመግባባቶችም በውይይት እንዲፈቱ በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን እድል ከመጠቀም ይልቅ አሁንም በሕገ-ወጥ ተግባራቸው መቀጠላቸውንመግለጫው አመልክቷል፡፡

መንግሥት በሀገሪቱ ብሎም በመዲናይቱ አዲስ አበባ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

የአማራ ክልል ጽንፈኛ ኃይሎች እና የሸኔ የሽብር ቡድን ታጣቂዎችን ሴራ ለማክሸፍ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀናጀ፣ጠንካራና ድንገተኛ ፍተሻ መካሄዱንና ከእነዚህ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በትብብር የሚሠሩ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር እንዲውሉ መደረጉን አመልክቷል፡፡

ለጊዜው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝም የተቀናጀ ክትትልና ስምሪት እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተካሄደ ድንገተኛ ፍተሻም ሰርገው ወደ ከተማዋ ከገቡ ፅንፈኞችና የሸኔ ሽብር ቡድን አባላት በርካታ የጦር መሣሪያዎች፣ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች፣ ቦንቦችና የሬዲዮ መገናኛዎችም ጭምር መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

አንዳንድ የውጭ ኃይሎች በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላም እያወኩ ያሉ ጽንፈኛ ኃይሎችንና ሽብርተኛውን ሸኔን እየደገፉ ሀገርን ለማፍረስ እያደረጉ ያለውን እኩይ ሴራ ግብረ -ኃይሉ ደርሶበታል ብሏል መግለጫው።

ይህንንም ለማክሸፍ ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛልም ብሏል።

የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል እየተንቀሳቀሱ ያሉ የውስጥና የውጭ ፀረ- ሰላም ኃይሎችና ቡድኖች ባሰቡት ልክ ወደ ተግባር እንዳይገቡና ፍላጎታቸው እንዲገታ እየተደረገ ባለው ስምሪት ተጋላጭነትን ቀድሞ በማወቅ ሊደርሱ የነበሩ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን ማስቀረት ተችሏል ብሏል፡፡

በሂደቱም የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የነበራቸው ትብብር እንዲሁም ተቀናጅቶና ተናቦ የመሥራት ባህል የላቀ እንደነበር አመልክቷል።

ኦፕሬሽኖች እንዲሳኩ ሰላም ወዳዱ ሕዝብ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሕዝብ ፀጉረ ልውጦችን፣ ሽብርተኞችንና ሕገ-ወጦችን አጋልጦ በመስጠት ያሳያው ተሳትፎ የሚደነቅ በመሆኑ ለዚህም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በቀጣይም የእነዚህን ፅንፈኛ ኃይሎች እና የሽብር ቡድኖችን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ በኩል እየተወሰዱ ያሉ ሕግን የማስከበር እርምጃዎችን በመደገፍና ወንጀለኞችን በማጋለጥ ረገድ ኅብረተሰቡ ሲሰጥ የነበረውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ- ግብረ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል።

የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል

ኅዳር 27/2016 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.