Fana: At a Speed of Life!

በሕገ-ወጥ መንገድ መሬት በመሥጠትና በመሸጥ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ መንገድ 1ሺህ 800 ካሬ ሜትር ይዞታን ለግለሰቦች በመሥጠትና ተቀብሎ በመሸጥ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የተባሉ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አማካሪን ጨምሮ 24 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና የወንጀል ችሎት ነው።

የፌዴራል ፍትኅ ሚኒስቴር የሙሥና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ሥልጣንን ያለ አግባብ መገልገል በሚል ከባድ የሙሥና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች አጠቃላይ ቁጥር 24 ነው።

ተከሳሾቹ የንፋስ ሥልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 01 ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፈይሳ ኒዳ ቡታ ፣ የንፋስ ሥልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 01 የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ክፍለ ከተማ የካሳ ግምትና ምትክ ባለሙያ ተክላይ ገ/ሕይወት፣ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽ/ቤት የካሳ ግምትና ምትክ ባለሙያ አፈወርቅ ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ የመሬት ልማት ከተማ ማደስ ጽ/ቤት የካሳ ግምት እና ምትክ አረጋጋጭ ቴዎድሮስ ግርማ እንዲሁም የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አማካሪ ቶሎሳ ተሥፋዬን ጨምሮ 11 የከተማ አሥተዳደሩ ሠራተኞችና 13 ግለሰቦች ናቸው።

ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ) ፣ንዑስ ቁጥር 3 እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና (ለ) እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተጠቀሰውን ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብለው ነው ክስ የቀረበባቸው።

በዚህ በቀረበባቸው ክስ እንደተመላከተው፡-

ከ1ኛ እስከ 9ኛ እንዲሁም 23ኛ እና 24ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱት ተከሳሾች የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ተመድበው ሲሰሩ በልዩ ወንጀል አድራጊነት የሙስና ወንጀል ተካፋይ ከሆኑት ከ10ኛ እስከ 22ኛ ከተጠቀሱት በግል ሥራ ከሚተዳደሩት ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ለሌላ ሰውም ለማስገኘት በማሰብ፣ ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ/ም እስከ ሕዳር 14 ቀን 2015 ዓ/ም ባሉት የተለያዩ ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አግባብ ባለዉ አካል ሳይፈቀድ የተያዙ ቦታወችን ከ10ኛ እስከ 18ኛ ተራ ቁጥር ለተጠቀሱ ተከሳሾችና የዐቃቢ ህግ ምስክር ለሆኑ አንድ ግለሰብ በህገወጥ መንገድ መብት መፍጠራቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ የተጠቀሱት ግለሰቦቹ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ መሆናቸውንና ቤት ሰርተው እየኖሩ መሆኑን እንዲሁም ግብር በስማቸው መከፈሉ ማረጋገጥ ሲገባቸው እንዲሁም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል በሚለቀቁ መሬት ላይ ለሰፈረ ንብረት ስለሚከፈል ካሳና ምትክ ቦታ አሰጣጥ በአፈፃፀም መመሪያ ሊሟላ የሚገባዉ መስፈርቶችን ማረጋገጥ ሲገባቸው በግልፅ የተደነገገውን መመሪያ መተላለፋቸውን እና ያለአግባብ የልማት ተነሺ በሚል 1ሺህ 800 ካሬ ሜትር ይዞታን በተለያዩ መጠኖች ካሳና ምትክ በሚል ለግለሰቦቹ መስጠታቸውን ጠቅሶ ዐቃቤ-ህግ በክስ ዝርዝሩ ገልጿል።

ይዞታዎቹ በንፋስ ሥልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 01 እና በልደታ ክ/ከ ወረዳ 3 ሥር የሚገኙ ይዞታዎችን በልማት ተነሺ በሚል ምክንያት ካሳና ምትክ መብት በመፍጠርና የተለያዩ መጠኖችን ደግሞ ግለሰቦቹ ወስደው በመሸጥ የሚል በክሱ ዝርዝር ይገኝበታል።

በአጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት ተከሳሾቹ ለልማት ተነሺዎች ሊሰጥ የሚገባዉን ካሳ እና ቦታ በህገ ወጥ መንገድ እንዲወሰዱ በማድረግ እና ሌሎቹ ተከሳሾች ወስዶ በመሸጥ ለራሳቸዉ ከላይ በዝርዝር የተገለጸዉን የማይገባቸዉን ብልፅግና በማግኘታቸዉ እና በመንግስት ላይም የመሬቱ ሊዝ ዋጋ የሆነዉን እና ካሳ የተከፈለዉን 80 ሚሊየን 755 ሺህ 508 ብር ጉዳት እንዲደርስ በማድረጋቸዉን ዐቃቤ-ህግ ጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ የሙስና ወንጅል ተካፋይነት በፈፀሙት የስልጣን አላግባብ መገልገል የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ዐቃቤ-ሕግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሠነድ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።

ተከሳሾቹ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጎ ለፊታችን ሰኞ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.