Fana: At a Speed of Life!

የመንግሥት ተቋማት የሀገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ አቅጣጫ መቀመጡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥት ተቋማት የሀገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ የሚያደርግ አቅጣጫ መቀመጡን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ የግልና የማኅበራት አምራች ኢንዱስትሪዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በዚህም የቡልኮ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር፣ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ፣ የፎንተኒና ቆዳ ፋብሪካ፣ የአዳል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል የወረቀት ፋብሪካና የኢትዮጵያ ልህቀት ማዕከል ተጎብኝተዋል።

ከመስክ ምልከታው በኋላ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደገለጹት ፥ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚል ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል።

“በኢትዮጵያ ታምርት” እንቅስቃሴ ምርት በስፋት እንዲመረት ከማድረግ ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ነው የገለጹት።

በማምረት አቅማቸው ዝቅ ብለው የነበሩትን ደግሞ የመደገፍ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

አሁን ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርትን በሀገር ውስጥ የመጠቀም ባህልን ለማሳደግና ዘርፉን በማጠናከር ሀገሪቱ ከዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ይህንንም ተከትሎ በተለይም የመንግሥት ተቋማት የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀሙ አቅጣጫ መቀመጡን ሚኒስትሩ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ(ዶ/ር) በበኩላቸው ፥ የመስክ ምልከታው በሪፖርት የቀረበልንን መሬት ላይ መኖሩን እንድናረጋግጥ አስችሎናል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቁመው በቀጣይም ተግባራቱ መጠናከር እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

ቋሚ ኮሚቴው ለዘርፉ ተዋናዮች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሕግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ ይሰራልም ብለዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.