Fana: At a Speed of Life!

ከ245 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከሕዳር 21 እስከ ሕዳር 27/2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከ245 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል 146 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 98 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የወጭ፤ በድምሩ 245 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዙን አስታውቋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች እንደሚገኙበትም ነው የተነገረው፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ጅግጅጋ፣ ድሬድዋ እና ሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ በቅደም ተከተላቸውም 84 ሚሊየን፣ 40 ሚሊየን እና 34 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ተችሏል መባሉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 16 ተጠርጣሪዎች እና አምስት ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉም ተጠቁሟል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝባች ምስጋና አቅርቦ ድርጊቱን ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት የመከላከል ስራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.