Fana: At a Speed of Life!

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትየጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ።

ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ መከላከል ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል።

ሥልጠናው በዋናነት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ምንነት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ባህሪያት፣ እውነትን ማጣራት የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ፥ ባለሥልጣኑ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ የሃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ሥርጭትን መከላከል የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጫ ነው።

አሁን ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ በአንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚተላለፉ የሃሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች አብሮነትን የሚሸረሽሩ ግለሰቦችን ለተሳሳተ ውሳኔ የሚያጋልጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም እነዚህን ድርጊቶች ለመከላከል በተለይም ታዳጊ ተማሪዎች ሃሰተኛ መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን የመለየት የመከላከል ክህሎትን በመጨበጥ እንዳይሰራጭ በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት።

ባለሥልጣኑ ያዘጋጀው ሥልጠናም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይህንን እንዲያውቁና እንዲከላከሉ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ራስን ከጥላቻ በማጽዳት አብሮነት የተጠናከረባት ሀገር መገንባት እንደሚገባ ገልጸው ፥ በዚህ ሂደት በተለይም ወጣቱ ትውልድ ለሀገር ግንባታ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ሊሆን እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።

ሥልጠናው በቀጣዮቹ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዘገበው ኢዜአ ነው።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.