Fana: At a Speed of Life!

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የበረሃ አንበጣና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተባዮች ፈተና ሆነዋል- ኢጋድ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የበረሃ አንበጣና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ተባዮች ለምስራቅ አፍሪካ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ጥረት ፈተና መሆናቸውን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ- መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ አስታወቀ፡፡

የኢጋድ የአየር ትንበያና ትግበራ ማዕከል ቀጣይነት ያለው ድንበር ተሻጋሪ የትንኞች (ተባዮች) አስተዳደር ፕሮግራም ዋና ተጠሪ ኬኔት ሙዋንጊ እንደገለጹት÷ በምስራቅ አፍሪካ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል፡፡

“አሁን ላይ አካባቢው በአረንጓዴ ተክል መሸፈኑ ለአንበጣ መስፋፋት አመቺ በመሆኑ እኛን ያሰጋናል፤ ከፍተኛ ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ በርካታ ተክሎች በማበባቸው ለአንበጣ መፈልፈል ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል” ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣይ አንበጣና ሌሎችም የሰብል አውዳሚ ተባዮች መስፋፋት ስለሚያሰጋ በኢጋድ አባል አገራት ቀጣናውን ማዕከል ያደረገ የመከላከል ሥራ ሊያከናውኑ እንዲገባ ገልጸው ማዕከሉ የአንበጣ መንጋ የሚራባበትን ቦታ በመለየት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በኢጋድ የአየር ፀባይ ትንበያ ማዕከል የአየር ፀባይ ለውጥ ሳይንቲስት የሆኑት ሄርበረት ኦሞንዲ ሚሳኒ በበኩላቸው÷ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከአንበጣ መንጋ በተጨማሪ በጎርፍ፣ ድርቅና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች በመፈተን ላይ ይገኛል ብለዋል።

“የመጪው ጊዜ ትንበያ የሚያሳየንም የድርቅ አደጋው በርካታ ተባዮች እንዲፈለፈሉና በሽታዎች እንዲስፋፉ ሊያደርግ እንደሚችል ነው” ያሉ ሲሆን÷በመሆኑም ኢጋድና አባል አገራቱ በመተባበር ችግሩን መከላከል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ፀባይ ለውጥን ለመከላከል የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የተጀመረ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ ልማት ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት ሌሎች የቀጣናው አገራት እንዲከተሉት አስገንዝበዋል።

በኢጋድ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ አሰልጣኝ የሆኑት ኢሳቅ ሳጋላ፤ ድንበር ተሻጋሪ የአንበጣ መስፋፋትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት መገናኛ ብዙኃን ለመንግሥታትና ለሚመለከታቸው አካላት መረጃ በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.