Fana: At a Speed of Life!

58 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2012 (ኢፍ.ቢ.ሲ) የትራንስፖርት ሚኒስትር ድኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የስራ ሃላፊዎች 58 ነጥብ 8ኪ.ሜትር የሚሸፍነውን የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ የመንገድ ግንባታ ግንባታን ዛሬ ጎበኙ።
 
የመንገድ ፕሮጀክቱን ቀደም ብሎ በወሰን ማስከበር እና ተያያዥ ችግሮች ሳቢያ በእቅዱ መሰረት ለማከናወን አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ ተጠቅሶ፥ በአሁኑ ወቅትም ያሉበት ዋና ዋና ችግሮች በመቀረፋቸው ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ በመከናወን ላይ መሆኑን ተገልጿል።
 
በዚህም በአሁኑ ወቅት የአስፋልት ማንጠፍ ስራ የተጀመረ ሲሆን፥ በያዝነው አመት መጨረሻ ድረስም ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ለማከናወን አቅዶ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል። አጠቃላይ ፕሮጀክቱን በቀጣይ አመት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ይሆናልም ነው የተባለው።
 
በዚሁ ወቅት ሚኒስትር ድኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ፥ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ያልተፈቱ ችግሮችን ለማቃለል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይበልጥ ተቀራርቦ እንዲሰራ አሳስበዋል።
 
የዛሬው የመስክ ቅኘት አላማም የፕሮጀክቱን ሂደት በአካል ከመመልከት ባለፈ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታትም ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።
 
የሙከጡሪ -ኮከብ መስክ መንገድ ከዚህ ቀደም በጠጠር ደረጃ የነበረ ሲሆን፥ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ አንጻር በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እንዲገነባ ነው።
 
በዚህም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።
 
የመንገዱ ግንባታ ከ768 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ጨረታውን አሸንፎ ግንባታውን በማከናወን ላይ የሚገኘው ቻይና ሪልዌይ ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪንግ ግሩፕ መሆኑ ተገልጿል።
 
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ተገንብቶ ሲጠናቀቅ አካባቢው ለምና የቱሪስት መስህብ ቦታዎች ስላሉት ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም ባለፈ ለመስመሩ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍይዳዎችን የሚያጎናጽፍ ነውም ነው የተባለው።
 
ከዚያም ባለፈ በመንገዱ የሚዋሰኑ የኦሮሚያና የአማራ ክልል አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀላሉና በተቀላጠፈ ሁኔታ ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ለማመላለስ እንደሚያስችል ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.