Fana: At a Speed of Life!

በድንበር በኩል የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር ከፌደራል መንግስት እና ከፀጥታ አካለት ጋር እየሰሩ መሆኑን የሶማሌ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከጎረቤት ሀገራት በድንበር በኩል የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር ከፌደራል መንግስት እና ከፀጥታ አካለት ጋር እየሰሩ መሆኑን የሶማሌ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አስታወቁ።

የሶሜሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሰተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ በድንበር አካባቢ ያሉ መግቢያዎችን ለመዝጋት እና ቁጥጥሩን ለማጠናከር ስራዎች በጥብቅ እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየጨመረበት በሚገኘው ሶማሌ ክልል እስካሁን 84 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎችም ከኬኒያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ የመጡ መሆናቸውን ነው ገልፀዋል፡፡

አሁንም ክልሉ ከእነዚህ ጎረቤት ሀገራት ጋር የሚዋሰንባቸው ቦታዎች መስፋት ለቁጥጥር አመቺ እንዳይሆን አድርጎታልም ነው ያሉት።

ይህን ለመቅረፍም በድንበር አካባቢ ያሉ መግቢያዎችን ለመዝጋት እና ቁጥሩን ለማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙስ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያዋስኑ መግቢያ ድንብሮችን የመዝጋት ስራዎች ቢከናወኑም በእግራቸው አቋርጠው የሚገቡ መኖራቸው እና የስደተኞች ቁጥር መጨመር ስጋት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወደክልሉ ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰንባቸው ቦታዎች መስፋት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ወደ ክልሉ ዘልቀው እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

ክልሉ አሁንም እንደ ስጋት የሆነበት ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ ሾልከው የሚገቡ መኖራቸው እና በተለይም አርብቶ አደሮች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሰፋ እንቅስቃሴ መኖሩ መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም ክልሉ በርካታ ስደተኞች የሚኖሩበት መሆኑም ለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የሚገልፁት።

ክልሉም ከጎረቤት ሀገራት የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር ሲባል ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚዋሰንባቸውን ድንበሮች የዘጋ ቢሆንም አልመሀል በሚባለው ወይም በጉባ በኩል በተለይም ምሽትን ተገን አድርገው በጫካ የሚገቡ መኖራቸውን ነው የሚናገሩት።

ይህን ለመከላከል ሲባልም የፀጥታ አካላትን በማሰማራት ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.