Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የሚገኙ ስጋ በል አዕዋፋት ዝርያ እየተመናመነ መምጣቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የሚገኙ ስጋ በል አዕዋፋት ዝርያ እየተመናመነ መምጣቱን በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች አመላከቱ፡፡

የተለያዩ የንስር ዝርያዎች፣ ጭልፊቶች፣ የሎሶች እና ጥንብአንሳዎች ባለፉት 40 ዓመታት ዝርያቸው የተመናመኑ ስጋ በል አዕዋፋት መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በአፍሪካ በህዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት ጫካዎች እና ዱሮች ወደ እርሻ መሬትነት መቀየራቸው ለአዕዋፋቱ ዝርያ መመናመን ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ኔቸር ኢኮሎጂ ኤንድ ኢቮሉሽን በተሰኘው መፅሄት ላይ የታተመው ጥናት እንዳመላከተው÷ ከ42 አዳኝ እና ስጋ በል የአዕዋፋት ዝርያ 90 በመቶ ያህሉ ቁጥራቸው ቀንሷል፡፡

ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት የአዕዋፋት ዝርያዎች ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጥፋት ስጋት እንደተጋረጠባቸው ነው የተገለፀው፡፡

ቀበሮዎችን፣ እባቦችን፣ አይጥና ትናንሽ ወፎችን በማደን የሚመገቡት እነዚህ ስጋ በል አዳኝ አዕዋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ በመምጣቱ አሁን ላይ በብሔራዊ ፓርኮች እና በጥብቅ ስፍራዎች ብቻ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የስጋ በል አዕዋፋት ዝርያ መቀነስ በሰው ልጆች ላይ አዲስ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል ያመላከተው ጥናቱ፤ በአዕዋፋቱ ዝርያ መመናመን በሰዎች ላይ እንደ ራቢስ እና የመሳሰሉ ቫይረሶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ማሳሰቡን ዘጋረዲያን አስነብቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.