Fana: At a Speed of Life!

የህጻናት የቆዳ አስም ምንነትና መንስኤ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህጻናት የቆዳ አስም በተለያዩ ምክንያቶች የህፃናት ቆዳ በሚቆጣ ጊዜ የሚፈጠር ህመም ነው፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ቃል ኪዳን ቤዛ÷ ህመሙ በብዛት ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ የመከሰት እድሉ ሰፊ ቢሆንም በየትኛውም እድሜ ክልል ውስጥ ያለ ህፃን በህመሙ ሊጠቃ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የህመሙ መንስዔ ወይም ቀስቃሽ ምክንያቶች የቆዳ ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች እና ኬሚካሎች መጋለጥ ናቸው ብለዋል፡፡

በዚህም ከህክምና ባለሙያ ያልታዘዙ ህፃናትን የምንቀባቸው የተለያዩ ቅባቶች፣ እንቁላል፣ የለውዝ ቅቤ፣ ብርቱካን፣ ምግብ ላይ የሚጨመሩ የተለያዩ ቀለማት እና አቮካዶ ብዙ ጊዜ ቀስቃሽ ምክንያቶች ናቸው ተብሎ እንደሚታሰብ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ድመት፣ ውሻና ዶሮን የመሳሰሉ እንስሳቶች ከህፃናት ጋር በቅርብ ግንኙነት ካላቸው ይህ ህመም ሊነሳ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ነፍሳት ንክሻ በቀላሉ የህፃናት ቆዳ እንዲቆጣ እንደሚያደርግም የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስቱ ተናግረዋል፡፡

የህመሙ ጠቋሚ ምልክቶችም ጉንጭ አካባቢ መቅላት፣ ተደጋጋሚ ሽፍታ፣ እራስ ቅላቸው ላይ እንደ ቅርፊት የመሰለ ቢጫ ነገር መኖር ይጠቀሳሉ፡፡

ቶሎ ቶሎ ሰውነታቸውን ማጠብ እና ከታጠቡ በኋላ ሰውነታቸው ሳይደርቅ ማለስለሻዎችን መቀባት እና ከቀስቃሽ ነገሮች ህፃናትን ማራቅ ህመሙ እንዳይነሳ ለማድረግ መልካም እንደሆኑ መክረዋል፡፡

30 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት በእድሜ ዘመናቸው በህጻናት የቆዳ አስም ህመም የመጠቃት እድል አላቸው ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.