የቫይታሚን ዲ እጥረት ስለሚያስከትለው የጤና ዕክል ምን ያህል ያውቃሉ?
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ማለትም (ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች) በቫይታሚን ዲ እጥረት ሊጠቁ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በአብዛኛው የከተማ ነዋሪዎች ፀሐይ የመሞቅ ልምዳቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ለቪታሚን ዲ እጥረት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
የቫይታሚን ዲ እጥረት ከሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች መካከል÷ የወገብ ህመም፣ የነርቭ ህመም፣ የጡንቻ መዛልና መልፈስፈስ፣ የአንጎልና አዕምሮ ህመም (አልዛይመር፣ መልቲፕል እስክለሮሲስ እና ድባቴ) እንደሚገኙበት ይናገራሉ፡፡
በዋናነት ከፀሐይ ብርሃን እንዲሁም ከምግብ የሚገኘው ቪታሚን ዲ÷ ለአጥንት መጠንከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡
በቂ የፀሐይ ብርሃን በማግኘት አጥንትን ከመሰበር እና ከመሳሳት መከላከል የሚቻል ሲሆን÷ በተፈጥሮ የፀሐይ ብርሃን ለማያገኙ ሰዎች በምግብ አሊያም በመድሐኒት እንዲያገኙ ይደረጋል ይላሉ።
የቪታሚን ዲ እጥረት ሲኖር የነርቭ ኅዋሳት ሥራ ይስተጓጎላል፤ የነርቭ ኅዋሳት ለሚከውኑት ሥራ የሚያስፈልጋቸው ሆርሞኖች እንዲመረቱ ቪታሚን ዲ ትልቅ ድርሻ አለው ይላሉ ባለሙያዎቹ ሲያብራሩ፡፡ እነዚህ ሆርሞኖች ደግሞ ሰው እንዲደሰት ብሎም ጤናማ እሳቤ እንዲያመነጭ ይረዳሉ ነው የሚሉት፡፡
የቫይታሚን ዲ እጥረት የሐሳብ መጋጨትን ያስከትላል፤ በዚህም ሰዎች ወደ ድባቴና የተዛባ አዕምሯዊ መዋቅር ሊሸጋገሩ ይችላሉ፡፡
ጸሐይ በመሞቅ በቂ ቫይታሚን ዲ ማግኘትትና በቪታሚን ዲ እጥረት የሚከሰቱ የጤና ዕክሎችን መከላከል እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡
ፀሐይ በውስጡ ጠቃሚ እና ጎጂ ጨረራዎችን ስለያዘ ሲበዛ ለቆዳ ካንሰር ያጋልጣል የሚሉት ባለሙያዎቹ÷ ይህን ለመከላከልም የቀትር ፀሐይን አለመጠቀም ተመራጭ ነው ይላሉ።
በተጨማሪም ቪታሚን ዲ÷ የጡንቻ ጤንነትን በመጠበቅ፣ የጀርባ አጥንትን በማጠንከር ፣ የበሽታ መከላከያ ሥርዓትን አደራጅቶ ከህመም በመታደግ፣ የሥነ- አዕምሮ ጤናን በማስተካከል ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይጠቅሳሉ፡፡
ቪታሚን ዲን ለማግኘትም÷ የጠዋት አልያም የማታ ፀሐይን ያለልብስና ያለቅባት ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት በሳምንት ለአራት ቀናት መሞቅ ይመከራል መባሉን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡