Fana: At a Speed of Life!

በአማዞን ጫካ ውስጥ ጥንታዊ ከተማ ተገኘ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማዞን ጫካ ውስጥ ትልቅ ጥንታዊ ከተማ መገኘቱን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በደቡብ አሜሪካ አማዞን ጫካ ውስጥ ኖረው ይሆናል ተብሎ ይታመን የነበረው ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ኑሯቸውን የሚገፉ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡

ለሺህ ዓመታት ተደብቆ የቆየው የአሁኑ ግኝት ግን በአማዞን ስለሚኖሩ ሰዎች የምናውቀውን ታሪክ ሳይቀይር አይቀርም መባሉን ቢ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡

በምሥራቃዊ ኢኳዶር ኡፓኖ አካባቢ የሚገኙ ቤቶች እና አደባባዮች በሚያስደንቅ የመንገድ እና የመሬት ሥር መተላለፊያዎች ከጥንታዊው ከተማ ጋር የተገናኙ እንደነበርም ነው በዘገባው የተመላከተው፡፡

የግኝቱን ጥናት የመሩት በፈረንሳይ ብሔራዊ የሣይንስ እና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ስቴፈን ሮስታይን (ፕ/ር) እንዳሉት÷ ግኝቱ ከዚህ ቀደም ስለ ሥልጣኔ እና ባሕል ስናስብ ወደ አእምሯችን የሚመጣውን አውሮፓ – ተኮር ምልከታ መቀየር እንዳለብን የሚያሳይ ነው፡፡

ሌላው የጥናቱ ተሳታፊ አንቶይን ዶሪሰን በበኩላቸው ብዙ የዘመናችን ሰዎች ስለ አማዞን ሲያስቡ ÷ ጥቂት ምናልባትም ራቁታቸውን የሆኑና ጎጆ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በአእምሯቸው እንደሚመላለሱ ፤ ግኝቱ ግን ይህን ዕይታቸውን እንደሚቀይር አመላክተዋል፡፡

የተገኘው ጥንታዊው ከተማም ከ2 ሺህ 500 ዓመታት ገደማ በፊት ሳይቆረቆር እንዳልቀረ ጥናታዊ መላ-ምት ተሰጥቷል፡፡

ለ 1 ሺህ ዓመታት ያህልም ሰዎች ሳይኖሩበት እንዳልቀረ ተመራማሪዎች ተናግረዋል፡፡

ምን ያህል ሰዎች በከተማው ሲኖሩ ነበር የሚለውን በትክክል ለመገመት አስቸጋሪ ቢሆንም÷ ከ10 እስከ 100 ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በጥንታዊው ከተማ ሳይኖሩ እንዳልቀረ ተመራማሪዎች ጠቅሰዋል፡፡

ጥንታዊው ከተማ ለእሳተ-ገሞራ ተጋላጭ እንደነበረ የሚያሳዩ ምልክቶች የተገኙ ሲሆን÷ ምናልባትም የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት ሳያጠፋ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.