Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም አጋዥ የትምህርት መረጃዎችን በነጻ ማቅረቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እና መምህራን ትምህርታዊ መረጃዎችን በነፃ ማግኘት እንዲችሉ ማድረጉን አስታወቀ።

መረጃዎቹ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያዘ የገጽ ለገጽ ትምህርቶች መቋረጣቸውን ተከትሎ የተዘጋጁ መሆናቸውን በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አመላክቷል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና ተማሪዎች አጋዥ መረጃዎችን http://ndl.ethernet.edu.et/ የተሰኘ ድረ ገጽ ላይ በነጻ ማግኘት ይችላሉ ነው ያለው።

ድረ ገጹ ከግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ነው በኩባንያው የቀረበው።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ የኮሮና ወረርሽኝን የተመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎችን ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያገኝባቸውን ድረ ገጾች አዘጋጅቶ በነጻ ማቅረቡንም አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተማሪዎችና መምህራን ያለክፍያ በዲጂታል ቤተ መጽሐፍት እንዲጠቀሙ ተወስኗል።

የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና መቋረጡ ይታወቃል።

በዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የተቋረጠውን ትምህርት በቴክኖሎጂ አስደግፎ በኦንላይን ለማስቀጠል እየተሠራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ትምህርቱ በኦንላይን ሲቀርብ የተማሪዎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም በመገንዘብ በነፃ መጠቀም ለማስቻል ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየተሠራ መሆኑንም ገልጿል።

በዚህ መሠረት ከዛሬ ጀምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወዳዘጋጀው የዲጂታል ቤተ መጽሐፍት ተማሪዎችና መምህራን ገብተው ሲጠቀሙ ከክፍያ ነፃ እንዲሆን መወሰኑን ነው ያስታወቀው።

በኦንላይን ቤተ መጽሐፍቱ ከ80 ሺህ በላይ ማጣቀሻዎች፣ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሞጁሎች፣ በምስል የተደገፉ አጋዥ ማብራሪያዎች እንዲሁም የሁሉም የትምህርት ዓይነቶች መማሪዎች እንደሚገኙበትም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.