Fana: At a Speed of Life!

ጥቂት መድኃኒትን በትክክል ስላለመውሰድ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምርመራ ለተረጋገጠ በሽታ ትክክለኛው መድኃኒት ለታማሚው በጊዜና መጠን ሲሰጥና ታማሚውም መድኃኒቱን በትክክል ሲወስድ አግባባዊ የመድኃኒት አጠቃቀም ይባላል፡፡

በአንጻሩ በትክክል ተመርምሮ የትኛው ዓይነት በሽታ አምጪ ተህዋስ እንዳስከተለው ለማይታወቅ በሽታ፣ ከታዘዘው መጠን በታች (በላይ) ሲወሰድ፣ መወሰድ ከነበረበት ሠዓት ታልፎ ሲወሰድ፣ የታዘዘውን ጸረ-ተህዋስ መድኃኒት ሙሉ በሙሉ ሳይወስዱ ከቀረ (ከተቋረጠ) ወዘተ አግባባዊ የመድኃኒት አጠቃቀም የለም ይባላል፡፡

መድኃኒትን በአግባቡ አለመጠቀም ደግሞ የተለያዩ ጉዳቶች ሲኖሩት ከእነዚህ ችግሮች አንዱ የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድ ነው፡፡

ተህዋሲያን (ጀርሞች ) ጸረ -ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ይላመዳሉ ማለት ምን ማለት ነው?

የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድ ማለት ከዚህ ቀደም በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም ሆነ ለመከላከል ሲሰጥ የነበረው አንድ ጸረ-ተህዋስ መድኃኒት ሲሰጥ በነበረው መጠን ወይም ከዚያም በላይ የሰውነትዎ ሴሎች ሊቋቋሙት በሚችሉት መጠን ሁሉ ሲሰጥ ተህዋሲያኑ የማይሞቱ ወይም መራባትን የማያቆሙ እና ህመምተኛው ከህመሙ የማይፈወስ ከሆነ ተህዋሱ ከመድኃኒት ጋር ተላምዷል ይባላል፡፡

ሒደቱን የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድ ይባላል፡፡ስለሆነም መድኃኒቱን በተላመደ ተህዋስ የታመመ በሽተኛ ምንም እንኳን በሽታው በትክክል ታውቆ መድኃኒቱን እየወሰደ ቢሆንም ከበሽታው የማይፈወስ ይሆናል፡፡

ከበሽታ አምጪ ተህዋሲያን ጋር የሚላመዱት የትኞቹ የመድኃኒት ዓይነት ናቸው?

እዚህ ጋር መታየት ያለበት ነገር የአንድን መድኃኒት የሚወሰደውን መጠን እየጨመርን ስንሄድ ምላሹ በዚያው መጠን ከፍ የሚል ወይም ያንን መድኃኒት ካልወሰድን ከህመማችን የምንፈወስበት ጊዜ ይኖራል፡፡

ይህ ሒደት መቋቋም የሚባል ሲሆን ፥ ከጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ጋር የተገናኘ አለመሆኑን ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለምሳሌ የዚህ ዓይነት ባህሪ ከሚያሳዩ መድኃኒቶች ፥ የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችና የአዕምሮ ህመም መድኃኒቶች (የናርኮቲክ እና የሳይኮትሮፒክ መድኃኒቶች) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የመድኃኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ ሲባል ግን የሰውነት ሴሎች በሚቋቋሙት መጠን ሁሉ ሲሰጥ ከሕመም የማይፈወስ ሲሆኑ ነው፡፡

ይህም ማለት መጠንን መጨመር ወይም መድኃኒቱን መውሰድ ትርጉም አይኖረውም ማለት ነው፤ መድኃኒቱ ከጥቅም ውጭ ሆኗልና፡፡

የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድ የሚባለው ጀርሞች ከጸረ-ተህዋሲያን (ጸረ- ጀርም መድኃኒቶች) ጋር በመላመዳቸው ምክንያት የሚከሰት ችግር ብቻ ነው፡፡

ሁሉም የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ማለትም ጸረ-ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) መድኃኒቶች፣ ጸረ-ቫይረስ መድኃኒቶች፣ ጸረ ፈንገስ መድኃኒቶች እና ጸረ-ፐሮቶዝዋ በበሽታ አምጪ ጀርሞች ይለመዳሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.