Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሳተላይት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ እየገነባች ያለች ሀገር ናት – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሳተላይት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ እየገነባች ያለች ሀገር ናት ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተሰሩ ባሉት የሳተላይት፣ የድሮን ቴክኖሎጂ እና የአይ ሲ ቲ ዘርፍ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷በዩኒቨርሲቲው ያሉ ምሁራን አቅምን በማጎልበት በኢትዮጵያ ቀጣይ ልማት ላይ እያበረከቱ ያለውን የፈጠራና ክህሎት ማበልጸጊያ ተግባር የሚበረታታ ነው፡፡

ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በመግለጽ ኢትዮጵያ ማገኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ዓለም እየተለወጠች ያለው በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመሆኑ ኢትዮጵያም ልዩ ትኩረት በመስጠትና በማበልፀግ የኢኮኖሚ ጉዞን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የዜጎችን የኑሮ ዘይቤ መለወጥ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የሰው ልጅ ህይወትን አቅልለው የሚታዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በብዙ ውጣ ውረድ የመጡ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ላይ በውጭ ሀገር ያሰለጠናቸው ባለሙያዎች ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ለሀገራዊ እድገት የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለማ ጉታ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ተቋማቸውን በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በጥናትና ምርምር፣ በአቅም ግንባታ እና በማህበረሰብ አገልግሎት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በመድረኩ በግብርና እና በጤናው ዘርፍ አገልግሎት የድሮን ቴክኖሎጂን በማበልጸግ ለማህበረሰቡ አገልግሎት ለመስጠት የተሰሩ ሥራዎች ላይ ምክክር መካሄዱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ 2ኛውን ሳተላይት ለማምጠቅ የደረሰችበት ደረጃ፣ በዩኒቨርሲቲው የሳተላይት መሰረት ሥራዎች እና ሌሎች የፈጠራና ቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ተግባራት ላይም ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.