Fana: At a Speed of Life!

ፓርኪንሰን በሽታ ምንድነው?

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕሙማኑ ከቁጥጥራቸው ውጪ ሰውነታቸው እንዲንቀሳቀስ ወይም እንዲንቀጠቀጥ የሚያደርገው ህመም ፓርኪንሰን ይባላል፡፡

የአንጎል ውሥጣዊ ሥርዓት ላይ በሚከሰት መዛባት እንደሚመጣ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ህመም የተጋለጡ ሰዎች ሚዛናቸውን መጠበቅ ያቅታቸዋል፡፡

የህመሙ ምልክቶች

• ከእንቅስቃሴ ጋር የተገናኙ፡- መንቀጥቀጥ፣ የሰውነት መግረር፣ የሰውነት ሚዛን መሳት፣ ዘገምተኛ እንቅስቃሴ

• ከእንቅስቃሴ ጋር ያልተገናኙ፡- ድብርት፣ እንቅልፍ፣ ማጣት፣ ለመጻፍ መቸገር፣ ለመናገር መቸገር፣ የምራቅ መዝረብረብ፣ የሆድ ድርቀት፣ የማሽተት ችሎታ መቀነስ፣ ቅዠት እና ወዘተ

የፓርኪንሰን ህመም ምክንያቱ አይታወቅም ነገር ግን ብዙ አጋላጭ ሁኔታዎች ሚና ይጫወታሉ፡፡

እነዚህም ፡-

• እድሜ፡- በወጣት ፓርኪንሰን የመከሰት እድሉ አናሳ ሲሆን፥ በጎልማሳነት እና በእርጅና እድሜ ይጀምራል፡፡
በዚህም የበሽታው ተጋላጭነት በእድሜ የሚጨምር ሲሆን፥ ሰዎች በአብዛኛው ህመሙ 60 ዓመት እና ከዚያ በላይ ሲሆናቸው ይከሰታል፡፡

• ዘር፡- በጣም የቅርብ የሆነ ቤተሰብ በፓርኪንሰን ከተጠቃ የመያዝ እድል የሚጨምር እንደሆነ የሚገለጽ ቢሆንም ብዙ የቤተሰብ አባል በፓርኪንሰን የተጠቁ ሰዎች እስከሌሉ ድረስ የመጋለጥ እድሉ በጣም አናሳ ነው፡፡

• ጾታ፡- ወንዶች ከሴቶች በበለጠ ለፓርኪንሰን ይጋለጣሉ፡፡ ለመርዛማ ኬሚካል መጋለጥ፣ ለተደጋጋሚ ጸረ-አረምና ጸረ-ተባይ ኬሚካሎች መጋለጥ የፓርኪንሰን ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡

ፓርኪንሰንን መከላከል ይቻላል?

የፓርኪንሰን ህመም ምክንያቱ ስለማይታወቅ መከላከያ መንገዱም እስካሁን ምንም በግልጽ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡

የተወሰኑ ጥናቶች ቀጣይነት ያለው አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በፓርኪንሰን የመያዝ እድልን ይቀንሳል ተብሎ እንደሚገመት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.