Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ወደ ቡድን 7 እንድትመለስ አሜሪካ ያቀረበችው ጥሪ በአባል ሀገራቱ መካከል ልዩነትን ፈጥሯል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ ወደ ቡድን 7 አባል ሀገራት ዳግም ተመልሳ እንድትቀላቀል ያቀረቡትን ጥሪ የአባል ሀገራቱ መሪዎች ውድቅ ማድረጋቸው ተሰምቷል።

በአሜሪካ አዘጋጅነት በያዝነው ወር እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የቡድን 7 ሀገራት ጉባዔ እስከ ፊታችን መስከረም ወር ሊራዘም እንደሚችል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ቅዳሜ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ወቅት የስብሰባው መራዘም ከቡድን 7 አባል ሀገራት ወጥተው የቆዩትን ሩሲያን ጨምሮ ሌሎችንም ለመመለስ እንደሚረዳም አስታውቅዋል።

ባሳለፍነው እሁድም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በቡድን 7 አባል ሀገራት ስብሰሰባ ላይ ሊጋብዟቸው አንደሚፈልጉ እቅዳቸውን ገልፀውላቸዋል ነው የተባለው።

ሆኖም ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለፕሬዚዳንት ፑቲን ያቀረቡት ግብዣ ከካናዳ እና ብሪታንያ መሪዎች ተቃውሞ ገጥሞታል የተባለ ሲሆን፥ የሀገራቱ መሪዎች የሩሲያን ዳግም ወደ ቡድን 7 ሀገራት መመለስን እንደማይቀበሉ አስታውቅዋል።

ሩሲያ ከዚህ ቀደም ቡድን 8 ተብሎ የሚታወቀውን የአሁኑን የቡድን 7 አባል ሀገራትን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 ከክሬሚያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለቃ መውጣቷ ይታወሳል።

በዘንድሮው የቡድን 7 ሀገራት ስብሰባ ላይም የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን እና የብሪታንያ መሪዎች በትብብር ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.