Fana: At a Speed of Life!

የሚሊኒየም አዳራሽ ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሕሙማንን መቀበል ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣2012  ( ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሕሙማንን መቀበል ጀመረ።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን÷ ባለፉት ሁለት ወራት ማዕከሉን የማደራጀት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን   ገልጸዋል።

ማዕከሉ 40 የጽኑ ሕሙማን መኝታዎችና 1 ሺህ ጽኑ ያልሆኑ ሕሙማን ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት ይችላልም ነው ያሉት።

ጎን ለጎንም የላቦራቶሪ፣ የመድሃኒት ቤት፣ የጤና ባለሙያዎች ልብስ መቀየሪያ፣ መታጠቢያዎችና ሌሎች ክፍሎችም ተዘጋጅተዋል።

በማዕከሉ ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማንና ለጤና ባለሙያዎች አስፈላጊ ግብዓቶች መሟላታቸውንም ጠቅሰው÷ በተጓዳኝም ከማዕከሉ የጥበቃ ሠራተኞች ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ነርሶችና ዶክተሮች ሥልጠና መሰጠጡን ተናግረዋል።

በዚህም የማዕከሉ ዝግጅት ተጠናቆ ዛሬ ህሙማንን መቀበል መጀመሩን  የገለጹት ዶክተር እስማኤል ÷ በማዕከሉ ሕሙማን አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ፤ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ሠራተኞችም ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ትኩረት መሰጠቱንም አክለዋል።

በተለይም የአየር ሥርዓት ፍሰቱን ለማስተካከል የሚረዱ መሣሪያዎች መገጠማቸው ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አስረድተዋል።

ከማዕከሉ የሚወገዱ ፍሳሾች ለብቻ እንደሚወገዱና ደረቅ ቆሻሻዎችም በዘመናዊ መሣሪያ በመታገዝ የሚወገዱ መሆኑንም ዶክተር እስማኤል ተናግረዋል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ የኮቪድ-19 ማዕከላትን የመፍራት ሁኔታዎች መኖሩን የጠቆሙት ዶክተር እስማኤል ይህ አመለካከት ሊቀየር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ በማዕከሉ ለሕሙማን የጤና ትምህርቶችና የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ጭምር ለመሥጠት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡ የቫይረሱን ስርጭትና ተዛማችነት ከግምት በማስገባት የመከላከል ሥራውን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.