Fana: At a Speed of Life!

ስለ አጥንት ቅኝት ምርመራ አስፈላጊነት ምን ያህል ያውቃሉ?

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአጥንት ቅኝት ምርመራ ማለት የአጥንትን የጤና ሁኔታ ለማወቅ የሚደረግ ሂደት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

የምርመራ ሂደቱ እንዴት ይከናወናል?

የምርመራው ሂደት የሚከናወነው÷ አነስተኛ መጠን ያለው ጨረር አመንጪ ንጥረ-ነገር በመርፌ ወደ ደም ሥር በማስገባት ከውጭ በሚገኝ ጨረር ለቃሚ መሣሪያ አማካኝነት ሥርጭቱን በምስል በመከታተል መሆኑን ነው ባለሙያዎች የሚያስረዱት፡፡

ወደ ደም ሥር የገባው ንጥረ-ነገርም ወደ አጥንት ይደርስና ችግር ያለባቸውን ቦታዎች ያጎላል ይላሉ፡፡

ቅኝቱም ወደ 30 ደቂቃ ገደማ እንደሚወስድ ገልጸው÷ ሂደቱም የህመም ስሜት እንደሌለው ይናገራሉ፡፡

በአጥንት ቅኝት ምርመራ የሚለዩት ህመሞች የትኞቹ ናቸው?

የአጥንት ቅኝት ምርመራ ማድረግ÷ ስብራትን፣ የመገጣጠሚያ ህመምን፣ የፓጄትስ የአጥንት በሽታን፣ ከአጥንት የሚነሳ ካንሰርን፣ ከሌላ የሰውነት ክፍል ወደ አጥንት የተሰራጨ ካንሰርን እንዲሁም የአጥንት፣ የመገጣጠሚያ ቅየራ ኢንፌክሽንኖችን ጨምሮ የተለያዩ የአጥንት በሽታዎችን ለማወቅ ይረዳል ይላሉ፡፡

ከምርመራ በፊት ምን ማድረግ ይጠበቃል?

ምርመራ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ከምርመራው በፊት ለተወሰነ ጊዜ መጾም እንደሚያስፈልጋቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በተጨማሪም ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎች (ታካሚዎች) አለርጂ ካለባቸው፣ የቅርብ ጊዜ ቀዶ ጥገና ካደረጉ፣ የሚወስዱት መድኃኒት ካለ፣ ያረገዙ ወይም የሚያጠቡ ከሆኑ ምርመራውን ለሚያከናውነው ሐኪም ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ነው የሚሉት ባለሙያዎች፡፡

የአጥንት ቅኝት ምርመራ ተከናወነ በኋላ ምን ይመከራል?

ባለሙያዎች እንደሚሉት ከምርመራ በኋላ ምግብ በአግባቡ መመገብ፣ መድኃኒቶችን ሳያቆራርጡ መውሰድ፣ መደበኛ እንቅስቃሴዎችንም መቀጠል ያስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም ራዲዮአክቲቭ ንጥረ-ነገሩ ከሰውነት እንዲወጣ ስለሚያግዝ ፈሳሽ በርከት አድርጎ መውሰድ እንደሚመከርም ይገልጻሉ፡፡

የአጥንት ቅኝት ምርመራ በማድረግ የሚገኙ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

የአጥንት ቅኝት ምርመራ በማድረግ ወደ አጥንት የተሰራጨ የካንሰር በሽታን ቀደም ብሎ ማወቁ ፈጣን ሕክምና እንዲጀመር ያስችላል፡፡

ይህም ህመሙ የተወሳሰበ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ክትትል በማድረግ በታካሚው ላይ አወንታዊ ውጤት እንዲመጣ ይረዳል ይላሉ፡፡

በተጨማሪም ለተለያየ የካንሰር ዓይነት የሚሰጡ ሕክምናዎች የሚያሳዩትን ምላሽ ለመገምገም እንደሚረዳ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መረጃ አመላክቷል፡፡

ወደ አጥንት ሊሠራጩ ከሚችሉ የተለመዱ የካንሰር ዓይነቶች መካከልም÷ የፕሮስቴት ካንሰር፣ የጡት ካንሰር፣ የሳምባ ካንሰር፣ የታይሮይድ ካንሰር፣ የኩላሊት ካንሰር፣ የኮሎሬክታል ካንሰር እና የጣፊያ ካንሰር ይጠቀሳሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.