Fana: At a Speed of Life!

የኩፍኝ በሽታ ምልክቶችና መከላከያ መንገዶች

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩፍኝ በሽታ በክትባት መከላከል ከምንችላቸው በሽታዎች መካከል አንዱ ሲሆን በቫይረስ የሚጣና እና በአጭር ጊዜ ከባድ ህመምና ሞትን ሊያስከትል የሚችል በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፍ በሽታ ነው።

በሽታው ማንኛውንም ከዚህ በፊት በበሽታ ተይዘው የማያውቁና ያልተከተቡ በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የሚያጠቃ ሲሆን÷ ህፃናት በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቂዎች ናቸው፡፡

የኩፍኝ በሽታ መተላለፊያ መንገድ:¬-

የኩፍኝ በሽታ በዋናነት ከተንፈሻ አካል በሚወጣ እርጥበት አዘል ነጠብጣቦች ወይም በትንፋሽ ማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው፡፡

በበሽታው የተያዙ ሰዎች በሚያነጥሱና በሚያስሉበት ወቅት ከመተንፈሻ አካላቸው የሚወጣ እርጥበት አዘል ትንፋሽ በቀጥታ ወደ ሌሎች ሰዎች መተንፈሻ አካል በመግባት ወይም በእጃቸው ነክተው ከሌሎች ሰዎች ጋር ንክኪ ሲኖራቸው ቫይረሱ ያረፈባቸው ቦታዎች ወይም እቃዎች እጅ ነክቶ አፍ፣ አፍንጫ እና አይን በመንካት ይተላለፋል፡፡

የኩፍኝ በሽታ ዋና ዋና ምልክቶች:¬-

ከፍተኛ ትኩሳት፣ ሰውነትን ያዳረሰ ሽፍታ፣ ሳል፣ የንፍጥ መዝረብረብ፣ የአይን ህመም (መደፍረስ/መቅላት) ያሳያል፡፡

የኩፍኝ በሽታ የሚያስከትላቸው ውስብስብ የጤና ችግሮች ምንድናቸው?

ምንም እንኳ ብዙ ህፃናት ውስብስብ ወደ ሆነ የኩፍኝ በሽታ ደረጃ ሳይደርሱ መዳን የሚችሉ ቢሆንም አንድ ሶስተኛ የሚሆት የኩፍኝ ህሙማን ከሚከተሉት የጤና ችግሮች አንዱ እንደሚከሰትባቸው የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያመላክታል፡፡

እነሱም የሳንባ ምች፣ የአፍ መቁሰል፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ተቅማጥ፣ የላይኛው የመተንፈሻ አካል (የአየር ቧንቧ) መዘጋት፣ የጆሮ ህመም፣ አይነ ስውርነት (በተለይ የቫይታሚን ኤ እጥረት ባለባቸው)፣ በነፍሰጡር እናቶች ላይ ጽንስ መቋረጥ፣ የአንጎል መጎዳት (የአንጎል ህመም) እና ሞት ሲሆን ውስብስብነቱ ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ የበለጠ ይሆናል፡፡

የኩፍኝ በሽታ መከላከያ መንገዶች ምንድናቸው?

የኩፍኝ መከላከያ ክትባትን ሁለት ጊዜ መውሰድ፣ በመኖሪያ ስፍራ በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር ማድረግ፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ፣ የግል ንፅህናን መጠበቅ፣ አፍ፣ አፍንጫ እና አይንን ባልታጠበ እጅ አለንካት፣ የታመሙ ሰዎችን በቶሎ ወደ ህክምና ተቋማት መውሰድ ይጠቀሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.