Fana: At a Speed of Life!

የሳንባ ካንሰር ዋና ዋና አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 01፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳንባ ካንሰር ማለት በሳንባ ውስጥ የሚገኙ ህዋሳት ከመደበኛ ዕድገታቸውና ቁጥራቸው ውጪ ጤናማ ባልሆነ መልኩ መባዛት ነው፡፡

የሳንባ ካንሰር ከሳንባ ተነስቶ ወደ አንጎል እንዲሁም ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጭ ይችላል፡፡

ለመሆኑ የሳንባ ካንሰር ዋና ዋና አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

– ማጨስ፡- ለሳንባ ካንሰር ዋነኛ አጋላጭ ሁኔታ ነው፤ የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም ለሳንባ ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል፡፡

ደባል አጫሾችም (ሲጋራ በሚያጨሱ ሰዎች አካባቢ የሚገኙ) ለሳንባ ካንሰር የተጋለጡ ናቸው፡፡

ማንኛውም የዕድሜ ክልል ማጨስን ማቆም በሳንባ ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ሊቀንስ ይችላል፡፡

– የስራ ቦታ፡- በብዛት ከሚታወቁ የስራ ቦታ አጋላጭ ሁኔታዎች ውስጥ እንደ አስቤስቶስ፣ ሲሊካ፣ ራዶን፣ ከባድ ብረቶች፣ ፖሊሳይክሊክ እና ሃይድሮካርቦን የመሳሰሉ ኬሚካሎች ያሉባቸው የስራ ቦታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

– የአየር ብክለት፡- በቤት ውስጥ እንዲሁም ከቤት ውጪ የሚኖር የአየር ብክለት ለሳንባ ካንሰር ተጋላጭ ያደርጋል፡፡

በተለይም በቂ አየር በሌላቸው ቤቶች ውስጥ ከሰል፣ እንጨት እና ሌሎች ለማገዶ የምንጠቀማቸው ነገሮች የሚያወጡት ጭስ ሴቶችን ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

– የቤተሰብ ሁኔታ፡- የሳንባ ካንሰር በቤተሰብ ውስጥ በዘር የመተላለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

– የጨረር ህክምና፡- በተደጋጋሚ በደረት ላይ የሚደረግ የጨረር ምርመራ በሳንባ ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ከፍ ያደርጋል፡፡

በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩትን አጋላጭ ሁኔታዎች መቀነስ ወይም ማስወገድ የሳንባ ካንሰርን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

የሳንባ ካንሰር ዋና ዋና ምልክቶች ምንድናቸው?

ለረጅም ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ወይም በቀላሉ የማይጠፋ ሳል፣ የደረት ህመም፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ስንተነፍስ ድምጽ መኖር፣ ደም የቀላቀለ አክታ፣ በብዛት የሚሰማ የድካም ስሜት፣ ባልታወቀ ምክንያት ክብደት መቀነስ፣ በተደጋጋሚ ለሳንባ ምች መጋለጥ ይጠቀሳሉ፡፡

የሳንባ ካንሰር ሕክምና:-

የሳንባ ካንሰር እንደ ካንሰር አይነቱ እንዲሁም እንደሚገኝበት የስርጭት ደረጃ በብዙ መንገዶች ይታከማል፡፡

በዚህም በቀዶ ሕክምና፣ በኬሞቴራፒ፣ በጨረር ሕክምና እና በሌሎች ዘመናዊ ህክምናዎች ወይም በእነዚህ ሕክምናዎች ጥምረት መታከም ይችላል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.