ወደ መዲናዋ የገባ 44 ክላሽንኮቭ እና አንድ መትረየስ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የሌላ ተሽከርካሪን ሰሌዳ በመጠቀም በተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ 44 ክላሽንኮቭ እና አንድ መትረየስ የጦር መሳሪያ መያዙን አዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የኮልፌ ቀራኒዩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ ባደረገው ክትትል ነው በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2A 91959 አዲስ አበባ በቶዮታ ፒካፕ ተሽከርካሪ ውስጥ ሌላ ቅጥያ አካል በማዘጋጀትና በመደበቅ ወደ አዲስ አበባ የገባ 24 ታጣፊ፣ 20 ባለሰደፍ ክላሽ እና 65 የክላሽ ካርታ እንዲሁም አንድ መትረየስ መያዝ የተቻለው፡፡
ፖሊስ ባደረገው ምርመራና ፍተሻ የተሽከርካሪውን ትክክለኛ ሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 00909 ሲዳ (ሲዳማ) መኪና ውስጥ ማግኘቱን ገልፆ ነገር ግን ተጠርጣሪው የሌላ ተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2A 91959 በመጠቀም ወንጀሉን መፈፀሙን አረጋግጧል፡፡
የጦር መሳሪያዎቹን ሲያዘዋውር የተገኘ አንድ ተጠርጣሪ ተይዞ ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚከናወኑ ተግባራት ህብተሰቡ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡